ከአምስት ወር በኋላ የቆሼ አደጋ ተራፊዎች በስቃይ ላይ መሆናቸውን ተናገሩ፤ ለፕሬስ ተናግራችኋል በሚል እየተቀጡ ነው ተባለ

አባይ ሚዲያ ዜና
በወንድወሰን ተክሉ

በኮልፌ ቆሼ ሰፈር ከአምስት ወር በፊት ከቆሻሻ መደርመስ አደጋ የተረፉ ቤተሰቦች መንግስት ቃል የተገባላቸውን እና በእጁም ያስገባውን እርዳታ እስካሁን እንዳልደረሳቸው ተናገሩ።

ተራፊዎቹ አሁን በግዜያዊነት በተጠለሉበት ለጎበኛቸው የሪፖርተር ጋዜጠኛ ያሉበትን አስከፊ ችግር በገሀድ ያሳዩት ሲሆን ከባለስልጣናቱ ከሚደርስባቸው ቅጣት ፍራቻም ለጋዜጠኛው እየደረሰባቸው ያለውን ችግር በዝርዝር ለመግለጽ ፈቃደኞች እንዳልሆኑ ጋዜጠኛው በዘገባው ገልጿል።

በጠባብ ቤት ውስጥ ከ60 እስከ 90 ሰዎች ተፋፍገውና ተጨናንቀው በሚኖሩበት ግዜያዊ መጠለያ ሰፈር ላሉ የቆሼ አደጋ ተራፊዎች በመንግስት በኩል ሲሰጥ የነበረው እለታዊ የምግብ ራሽን “ለጋዜጠኞች መረጃ በመስጠት አጋልጣችሁናል” በሚል ቅጣት ካቋረጡባቸው ሁለተኛ ሳምንት መሙላቱንም ለማወቅ ተችሏል። ብዙዎቹም እያደር እንደጉም አልጨበጥ እያላቸው ላለው የመንግስት ተስፋ ቃል ተስፋ የቆረጡ ሲሆን ከህዝብ የተዋጣላቸውን እንኳን ሊሰጣቸው እንዳልፈቀደ መረዳት ተችሏል።

በኮልፌ ቆሼ ሰፈር እስከ አሁን ባልታወቀ ምክንያት በተፈጠረ የመሬት መንሸራተት ከ130 በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከአደጋው ለተረፉትም መልሶ ማቋቋሚያ ከህብረተሰቡ ከ107 ሚሊዮን ብር በላይ ብር መዋጣቱ የሚዘነጋ አይደለም።