ለረጅም ጊዜ በአሜሪካ የሩሲያ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት ሴርጌይ ኪስሊያክ አገልግሎታቸውን ፈጽመው ወደአገራቸው ተመለሱ

አባይ ሚዲያ ዜና
ጋሻው ገብሬ

ሲ ኤን ኤን ዛሬ ከአትላንታ እንደዘገበው የሩሲያው አምባሳደር ሴርጌይ ኪስሊያክ በአሜሪካ የቆይታ አገልግሎታቸውን ፈጸመው ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል።

አምባሳደር  ሴርጌይ ኪስሊያክ ለፕሬዚዳንት ዶናል ትራምፕ አሁን ባለው ውዝግብ ከመሃል ሆነው በቅርቡ ደጋግመው ሲነሱ ቆይተው ነበር። ውዝግቡ ፕሬዚዳንት ዶናል ትራምፕ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወቅት ተወዳዳሪያቸው ሂላሪ ክሊንተንን ለማሸነፍ በሚል በሚስጥር የሩሲያ መንግስት ጋር ዶልተዋል የሚል ነው። ውዝግቡ የትራምፕን ቤተሰብ ባለስልጣኖቻቸውን ያነካካ አሁንም እልባት ያላገኘ ጉዳይ ነው። በዚሁ ጉዳይ የፕሬዚዳንት ዶናል ትራምፕ ወንድ ልጃቸው በአሜሪካ ህዝብ ምክር ቤት ቀርቦ ሊጠየቅ ነገ ሰኞ ቀጠሮ ተይዟል።

ስለ አምባሳዶር ሴርጌይ ኪስሊያክ ግልጋሎት ዘመን አልቆ መሰናበት የሩሲያ ኤምባሲ የሚለው፣ ጉዳዩ ከወር በፊት ጀምሮ የታቀደ መሆኑን ነው። የሩሲያ መንግስት የአምባሳዶር  ሴርጌይ ኪስሊያክ ምትክ አናቶሊይ አንቶኖቭ እንደሚሆኑም ግልጿል።

አምባሳዶር ሴርጌይ ኪስሊያክ በምህድስና ትምህረት የሰለጠኑ 1977 የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን እንደተቀላቀሉ ተዘግቧል። ለመጀመሪያ ጊዜ አገራቸውን በአሜሪካ ያገለገሉት በ1985 እና 1989 መካከል ነበር። የሩሲያ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ህብረት (NATO) አምባሳደር በመሆን አገራቸውን አገልግለዋል።

የአምባሳዶር ሴርጌይ ኪስሊያክ ስም በዜና አውታሮች አፍ የገባው በጣም ላጭር ጊዜ የብሄራዊ ጸጥታ አማካሪ የነበሩት ጄኔራል ማይክል ፍሊን ጋር በምስጢር ተገናኝተዋል ተብሎ ዜናው በወጣ ወቅት ነበር። ጄኔራል ማይክል ፍሊን በፕሬዚዳንት ትራምፕ ከስራቸው የተወገዱ ናቸው። ዛሬ ተጨማሪ ውዝግብ  የፈጠረው አምባሳዶር ሴርጌይ ኪስሊያክ ከዶናል ትራምፕ የፍርድ ሚኒስትር ከሆኑት ዋናው ህግ አስከባሪ ጄፍ ሴሽን ጋር ግንኙነት ነበራቸው የሚለው ሚስጢር ሾልኮ ከወጣ ወዲህ ነው። ይህን ጉዳይ የአሜሪካ የስለላ ተቋም ደግሞ መረጃ አንዳለው እየገልጸ ነው።

አምባሳዶር ሴርጌይ ኪስሊያክ የ66 ዓመት እድሜ አላቸው። ለምን በዚህ ጊዜ ወደአገራቸው ተመለሱ የሚለው ጥያቄ ማነጋገሩ የማይቀር ነው። አምባሳደሩ “በስራቸው ትጉህ፣ የማንን አገር እንደሚወክሉ በግልጽ የሚታወቅ” ብለው ማይክል ማክፉል ይገልጿቸዋል። ማይክል ማክፉል በሩሲያ የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ናቸው።