ከአማራው ክልል ለእርቅ ወደ ትግራይ የሄዱት የክልሉን ሕዝብ የሚወክሉ አይደሉም ሲሉ ነዋሪዎች ገለጹ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ወደ ትግራይ ክልል የተጋዙት ከ400 በላይ የአማራ ክልል የብአዴን ባለስልጣናት፣ ካድሬዎችና የደህንነት ሰዎች የአማራውን ሕዝብ የገደሉ፣ ያስገደሉ እንጂ የሚወክሉን አይደሉም ሲሉ የክልሉ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ላለፉት ሶስት ቀናት በትግራይ ዋና ከተማ መቀሌ ከተማ ከትግራይና ከአማራ ክልል ከተውጣጡ 1500  በላይ ተሳታፊዎች የእርቅ ጉባኤ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በጉባኤው ላይ ለመገኘት ከአማራው ክልል የተጋዙት 400 ሰዎች ባለስልጣናት፣ ካድሬዎች፣ ሰላዮችና ሚሊሺያዎች እንጂ በህዝብ ተመርጠው የተላኩ ተወካዮቻችን አይደሉም ሲሉ ያነጋገርናቸው ሰዎች ተናግረዋል።

በወልቃይት የማንነት ጥያቄ ምክንያት በአማራ ክልል በተለይም በጎንደር እና በጎጃም በተነሳ ህዝባዊ ዓመጽ በመቶ የሚቆጠሩ የክልሉ ተወላጆች በግፍ በአግዓዚ ሰራዊት የተገደሉ ሲሆን በሺህ የሚቆጠሩትን ደግሞ በእስር ያጎረ ሲሆን በወቅቱ የስርዓቱ ደጋፊ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች በድርጊታቸው “ለህይወታችን እንሰጋለን” በማለት ክልሉን ለቀው ወደ መቀሌ መመለሳቸው የሚዘነጋ አይደለም።

በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራው ክልል ፕሬዚዳንት መሪነት ወደ ትግራይ የተጋዘው ቡድን በመቀሌ ከአቻው ዓባይ ወልዱ በሚመራ 1100 የትግራይ ተወካዮች በተሳተፉበት ሶስት ቀን የፈጀ ጉባኤ መካሄዱን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን ዋና ዓላማውም በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን ግጭት በእርቅ ሽምግልና ለመፍታት እንደሆነ ከወጣው መንግስታዊ መግለጫ ላይ ማወቅ ተችሏል።

በመቀሌው ስብሰባ ነውጠኛው እንደነ አቶ ስብሃት ነጋ አይነቶቹ “ብአዴን ወጥጧል መመታት አለበት” የሚል እድምታን ሲያራምዱ እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን የስብሰባው አጠቃላይ ይዘትም በአማራና ትግራይ ህዝብ መካከል እርቅ ለመፍጠር ሳይሆን በብአዴን ውስጥ የተፈጠረውን የጸረ-ህወሃት ሴል መጥሮ በፍጹም የህወሃት ታዝዦች ለመተካት እንደሆነ ነው መረዳት የተቻለው። ሆኖም ቀደም ሲል በሰሜን ጎንደር አርማጭሆ ሳንጃ የህወሃት ሰዎች የአካባቢውን ነዋሪዎች ሰብስበው የእርቅ ንግግር በጀመሩበት ወቅት ነዋሪው “ልጆቻችን እና ወገኖቻችን ታስረውና ተገድለው ምን ዓይነት እርቅ ነው” በሚል እንዳልተቀበላቸው ይታወቃል።

በዚህ ጉዳይ ፍላጎቱ ያልተሳካለት የህወሃት ስርዓት በአርማጭሆ የህዝብ ተወካዮች ብሎ 16 የስርዓቱን ሰላዮች፣ ካድሬዎችን መልምሎ እንደወሰደ ገልጸው በአጠቃላይ ከአማራው ክልል የተመረጡት የመቀሌው ጉባኤ ተወካዮች የአማራን እና የአካባቢውን ህዝብ የማይወክሉ የስርዓቱ አገልጋዮች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል። አይወክሉንም ካሏቸው ሰዎች ውስጥ ከአርማጮሆ የተወከሉ የተባሉትን የ16 ሰዎች ስም ዝርዝርና ማንነታቸውን የሚገልጽ ጽሁፍ እንዳሰራጩም ማወቅ ተችሏል።