የአውሮፓ ሕብረት፣አሜሪካና የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ወደ ኬኒያ እንደሚልኩ ታወቀ

አባይ ሚዲያ ዜና
በወንድወሰን ተክሉ

ከሁለት ሳምንት በሃላ ምርጫ በምታካሄደው ኬኒያ የአውሮፓ ህብረት ከመቶ በላይ ታዛቢ ቡድን እንደሚልክ ሲያስታውቅ አሜሪካ በበኩላ በቀድሞ የወጭ ጉዳይ ም/ር ጆን ኬሪ የሚመራ ታዛቢ ቡድን እንደምትልክ ማስታወቃቸው ተገለጽ።

ከፍተኛ ፉክክር ይካሄድበታል ተብሎ በተገመተው የኬኒያ ምርጫ ዓለም አቀፍ ትኩረት የሳበ በመሆኑ የአፍሪካ ሕብረትም በበኩሉ በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ እምቢኬ የሚመራ ታዛቢ ቡድን ወደ ኬኒያ እንደሚልክ ለመረዳት ተችላል።

የአምስት ፓርቲዎች ቅንጅት ውጤት የሆነውን ናሳ [NASA]እጩ አቶ ራይላ አሞሎ ኦዲንጋ እና ለሁለተኛ ዙር የሚወዳደሩት ፕሬዚዳንት ሁሩ ኬኒያታ መካከል ከፍተኛ ፉክክር ያለበት ምርጫ እንደሚፈጸም የታወቀ በመሆኑ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ልዩ ትኩረት ለመሳብ እንደቻለ የታወቀ ሲሆን ከኬኒያ በፊት የፊታችን ነሀሴ 3-4 ምርጫ ለምታካሂደው ሩዋንዳ ማንም ታዛቢ ለመላክ እንዳልፈቀደም መረዳት ተችላል።

ኬኒያ በ2010 ባጸደቀችው አዲሱ ሕገ-መንግስታ ስር ምርጫ ስታካሂድ ይህ የዘንድሮው ለሁለተኛ ግዜ ሲሆን የመጀመሪያው በ2013 ያካሄደችው ምርጫ ተቃዋሚው አቶ ራይላ ኦዲንጋ “ተጭበርብሬያለሁ” በማለት ውጤቱን አልቀበልም በማለታቸው ጉዳዩ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ በሰባት ዳኞች ችሎት የሁሩ ኬኒያታ አሸናፊነት በመወሰን የምርጫውን ውዝግብ መፍታታቸው የሚዘነጋ አይደለም።

ከ1997 ጀምሮ ለፕሬዚዳንትነት ሲወዳደሩ የሚታዩት ተቃዋሚው መሪ አቶ ራይላ ኦዲንጋ ዘንድሮ ለ4ኛ ግዜ የሚወዳደሩ በመሆናቸው የመጨረሻቸው ነው ተብሎ የተገለጸ በመሆኑ እሳቸውም በልዩ ዝግጅት እንደተዘጋጁበት መረዳት ተችላል።

የተቀዋሚው መሪ ባላቸው የዘንድሮውን ምርጫ የማሸነፍ ፍጹም ውሳኔ እና ባላቸው ብርቱና ጠንካራ ደጋፊዎቻቸው ምክንያት እጅግ የሚፈሩ ሲሆን በ2007 በተካሄደው ምርጫ የአሸናፊነትን ድምጽ አግኝተው ተቀባይነትን ባጡበት ወቅት በተነሳው ብጥብጥ ከ1300በላይ ኬኒያውን ህይወት መጥፋትና ከ600ሺህ በላይ ደግሞ መፈናቀል አደጋ መከሰቱ የሚዘነጋ አይደለም።

ኬኒያ በመጪው ነሀሴ 8 ቀን 2017 ለምታካሂደው ምርጫ የሀገሬውም ህዝብ በፍርሃትና በስጋት እንደሚያየው ከኬኒያውያኑ አንደበት የአባይ ሚዲያ ተወካይ መረዳት ችላል።