የግብር ሰብሳቢው ባለስልጣን እና የነጋዴው ማህበረሰብ እሰጥ-አገባ-ልዩ ዘገባ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

አቶ ከበደ ጫኔ በምኒስትር ማእረግ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር ሲሆን አቶ አዲሱ አረጋ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮምኒኬሽን ባለስልጣን ናቸው።

ሁለቱም ባለስልጣናት በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልሎች ገቢራዊ ተደርጎ ብዙ አመጽና ተቃውሞ የቀሰቀሰውን የግብር ተመን ስራን በተመለከተ ነጋዴው ማህብረሰብ ጥያቄውን እያቀረበ እኛም በአግባቡ እያሰተናገድን ነው በማለት ሲመልሱ ነጋዴው ማህበረሰብ በበኩሉ የለም የተመለሰም ሆነ የተስተካከለ ነገረ አላየንም ሲሉ የባለስልጣኑን አባባል ያጣጥላሉ።

ይህን መሰረት ያደረገና የሰሞኑን የንግዱ ማህበረሰብን ቅዋሜን የዳሰሰ ልዩ ጥንቅር እንደሚከተለው ተቀናብሯል-
**የንግዱ ማህብረሰብ ወቅታዊ ሁኔታ

በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍል ከተሞች የሚካሄደው የስራ ማቆም አድማ እረቡእ ቀጥሎ ታይቷል።በመርካቶ የተከሰተው የስራ ማቆም አድማ ሰኞና ማክሰኞን ተጠናክሮ ከተፈጸመ በኋላ እረቡእ እለት አብዛኞቹ ሱቆች ከፍተውና ወይም ታሽገው ታይተዋል።

በንፋስ ስልክ-ሳሪስ ኮልፌ ያሉት የንግድ መደብሮች በአድማው እንደቀጠሉ ናቸው። ከአዲስ አበባ ተሻግረን በአማራ ክልል ደጀን ከተማ በስራ ማቆም አድማው ከተማዋ በጭርታ ተጥለቅልቃ ታይታለች።ድርጊቱን ቀደም ሲል የምስራቅ ጎጃማ ሸበል በረንታ ከተማ እንደጀመረችው ይታወቃል። ሆኖም የአማራው ክልል በተለይም በጎንደር እና አካባቢው የግብሩ ተመን ይፋ እንዳይደረግ ባለስልጣናቱ ማዘዛቸው ይታወቃል።

በኦሮሚያ ክልል በተለይም በምእራብ ኦሮሚያ ግዛቶች የስራ ማቆም አድማ ተጠናክሮ ቀጥሏል ወይም ወደ ስራ መመለሱ ሙሉ በሙሉ ተተግብሮ ማየት አልተቻለም።

ባለስልጣናት በየአካባቢው የንግዱን ማህበረሰብ በማሰባሰብ ንግግር እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። የተጠቀሰው ንግግር መከሰቱን ነጋዴዎቹም ይስማሙበታል። ሆኖም ነጋዴዎቹ ሲስማሙበት ያላየነው ነገር ቢኖር ከባለስልጣናቱ የነጋዴውን ቅሬታ እየሰማን እና እየፈታነው ነው በሚለው አባባል ነው።ባለስልጣናቱ እየፈታን ነው ሲሉ ነጋዴዎቹ ደግሞ የለም የተፈታና እየተፈታ ያለ ነገር አላየንም ባይ ናቸው።

**የሚፈታው ችግር ምንድነው? በእርግጥስ ይፈታል?ተፈቷልስ?

የሁለቱ ባለስልጣናት የእለት ተእለት ገቢ ግብር ተመነን ችግር አገላለጽ እራሱ እርሰ በርሱ የሚጣረስ ሆኖ አግኝተነዋል።
እንደ የኦሮሚያው ባለስልጣን አቶ አዲሱ አረጋ አገላለጽ መንግስት ሳይንሳዊ በሆነ የአሰራር ዘዴ በመጠቀም የግብሩን መጠን መተመን መቻሉን በመግለጽ የተተመነውን ግብር ፍትሃዊነትን ሲገልጹ እንደ አቶ ከበደ ጫኔ አገላለጽ ደግሞ መንግስት የእለት ተእለት ገቢ ተመንን በሳይሳዊ መንገድ ያልተመነው መሆኑን በመግለጽ ችግር ሊኖር ስለመቻሉ እውቅና ሰጥተው ሲናገሩ ይሰማሉ።

የሆነው ሆኖ በሳይንሳዊ መንገድ ተተመነ ወይም በኢ-ሳይንሳዊ መንገድ ተተመነ ቁም ነገሩ የዘንድሮው 2009 የግብር ተመን ኢ-ፍትሃዊ በመሆኑ ምክንያት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ ህዝባዊ ተቃውሞና አመጽ መቀስቀስ መቻሉ ጉዳይ ላይ ነው የምናተኩረው።

እንደ አቶ አዲሱ አረጋ አገላለጽ እስከ አሁን ከ80ሺህ በላይ ነጋዴዎች አቤቱታ አቅርበው ለ11ሺህ ያህሉ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ መቻላቸውን ገልጸው በተቀሩት አመልካቾችም ላይ ተመሳሳይ የማስተካከያ እርምጃ ስለምንሰጥ ነጋዴው ማህበረሰብ የስራ ማቆም አድማውን በማቆም ወደ ስራው እንዲሰማራ የሚያሳስብ ሲሆን ከሻምቡ፣ጊንጪ፣አምቦ፣ወሊሶ፣ኦሎንኮሚ ነቀምት፣ጉደር፣ደምቢዶሎ፣አርጆጅማ፣ጀልዱ፣ሽኩቴ እና በሰሜን ኦሮሚያ ፍቼ፣ገብረ ጉራቻ ያሉት ነጋዴዎች ደግሞ አይደለም ማስተካከያ እርምጃ ሊሰጠን ቀርቶ በተሰበሰብንበት ስብሰባ ላይ ተነግራችኋል የተባሉ ነጋዴዎች እየታፈኑ ታስረውብናል ሲሉ ይናገራሉ።

በአዲስ አበባ የንፋስ ስልክ፣ኮልፌ አጣና ተራና የመርካቶ ነጋዴዎች የባለስልጣኑን አቶ ከበደ ጫኔን መግለጫ የሚጣረስ መልስ “እኛ ያየነው የማሻሻያ እርምጃ አላየንም። መንግስት በመገናኛ ብዙሃን ቅሬታ ላቀረበ መልስ እየሰጠሁ ነኝ ያለውን ሰምተን ወደ ቢሮዋቸው ስንሄድ የምናየው ግን የተገላቢጦሽ ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

ነጋዴዎቹ ይህንን ሲያስረዱም ቅሬታ ይታይላችኋል ማለት የተተመነብንን ግማሽ ከፍለን የቅሬታ መሙያ ቅጽ ይሰጠናል ማለት ነው ካሉ በሃላ ያንን ደግሞ ክፍያ ፈጸምን ማለት የግብር ደረጃችን ከምድብ “ሐ” ወደ ምድብ “ለ” ያሸጋግረናል ባይ ናቸው።

በምድብ “ሐ”የተመደቡ የእለት ተእለት ገቢ ነጋዴዎች ለዓመታት ከ300 እስከ 2500 ብር ሲከፍሉ የነበረው ዓመታዊ የግብር ተመን ድንገት ተመንድጎ ከ17000-65000ብር እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን ገልጸው ቅሬታችንን ለመሰማት ክፈሉ የተባለነውን ግማሽ ተመን ብንከፍል እንኳን አሁንም እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ መክፈል የማንችል ከመሆናችንም በላይ ደረጃችንን ወደ ምድብ “ለ” ክፍ ያደርግብናል ባይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊው መንግስት ለ2010 ዓ.ም ዓመታዊ በጀት ከ320ቢሊዮን ብር በላይ የበጀተ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ወደ መቶ ቢሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ጉድለት እንዳለውና ጉድለቱንም ከሀገር ውስጥ አበዳሪዎች ተበድሮ ለመሙላት ማቀዱን መግለጻችን አይዘነጋም።

ከዚህ ጎን ለጎን ተያያዥነት ያላቸው የጸጥታ ችግር ምክንያት መንግስት ሲያገኝ የነበረው ገቢ በአብዛኛው የመቀነስና ብሎም የመመናመን ሁኔታ በማሳየቱ የወጠናቸውን ግዙፍ ፕሮጄክቶችና መንግስታዊ ስራዎቹን በአግባቡ ለመፈጸም ላጋጠመው ከፍተኛ የበጀት ክፍተት ስንመለከት የግብሩን ተመን እንዲሁ በዋዛ ይቀንሳል ብሎ መጠበቁና መገመቱ የዋህነት እንደሆነ ሁኔታው ያሳያል።

በዚህም ምክንያት ነጋዴው ማህበረሰብ ኢ-ፍትሃዊ የሆነውን የግብር ተመን ለማስለወጥ ያላወላወለ ረዥም ግዜ የሚጠይቅ የተቃውሞ የስራ አድማ በተባበረ መልኩ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲያደርግ የሚያስገድድ ሁኔታን እንደተጋፈጠ መረዳት እንችላለን።