ከበደ ሃይለማርያም በቫንኩበር የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ አምባሳደር

[በወንድወሰን ተክሉ]

“ከበደን ከ18 ዓመት በላይ አውቀዋለሁ። ወደ ቫንኮበር በመምጣት እኔ ብቀድመውም ወደ ኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በመግባትና በሃላፊነትም እንዲንቀሳቀስ በመመረጥ ግን እሱ ይቀድመኛል። በወቅቱ ማህበራችን እጅግ ተዳክሞና ለመፈራረስ ደረጃ ላይ ተዳርሶ ነበር። ከበደ ገና ለቫንኩበር እንግዳ ቢሆንም በኬኒያ ቆይታው የሚያውቁት መመረጥ አለበት በማለት ጥቆማ ሰጡ እናም እንዳሉትም ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይል ማህበሩን በማጠናከር ስራ ላይ ተጠመደ..” አቶ ኦሪዮን መንግስቴ የአቶ ከበደ ሃይለማርያም የረዥም ዘመን የቅርብ ወዳጅና ባልደረባ።

ኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያዊ አንድነት የዚህ ጽሁፍ ዋና አስኳል ነው። ከወደ ቫንኩበር የኢትዮጵያዊነትን ስሜትና ሃላፊነትን በጉልህ እየተወጡ ያሉ በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን አሉ። አቶ ከበደ ሃይለማርያም አባተ አንዱ ነው–

image
“በሲያትሉ የኢትዮጵያውያን ፌስቲቫል ላይ አቶ ከበደ ከኢትዮጵያዊታ የቦን-ማሮው እርዳታ ፈላጊ ኤልሳ ድንኳን ሆኖ በከፍተኛ ድምጽ እባካችሁ ወገናችንን እንርዳት እያለ በመጣራት ስራ ተጠምዶ ነበር።ለቫንኮበሩ ፌስቲቫላችን በማስተዋወቅም ተወጥሮ ነበር።ብቻ አቶ ከበደን ባየሁ ቁጥር እንደ እድሜው ሳይሆን እንደ ታናሻችን ሆኖ በSelfless ትጋት ሲታዘዝና ሲፈጽም ነው የማውቀው..” ወ/ሮ ናኒ ተስፋዪ ታደሰ በ2017ቱ የቫንኮበር ኢትዮጵያውያን ፌስቲቫል አዘጋጅ ኮሚቴ አባልነቷ ስለ አቶ ከበደ ያየችውን ስትናገር።

“ማህበሩን እንዲመሩ ከመረጥናቸው ሰባት የኮሚቴ አመራር አባላት ውስጥ ስድስቱም ስራቸውን ጥለው በነበረበት ወቅት አቶ ከበደ ብቻውን ሃላፊነቱን እና የሌሎቹንም ሃላፊነት በመወጣት ማህበሩን ከመፍረስ አድኖ ማህበሩ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ በማድረስ ትልቁን ሚና የተጫወተ በመሆኑ ስሙ ሊጠቀስና ሊመሰገን ይገባል” ያለኝ ደግሞ አቶ ደበበ ጋሉ በቫንኮበር የኢትዮጵያን ማህበረሰብ ማህበር ሊ/መንበር የነበረና በዘንድሮው የበጋ ፌስቲቫል አዘጋጅ ኮሚቴ አባል የሆነ ኢትዮጵያዊ ነው ስለ አቶ ከበደ የሚያውቀውን የነገረኝ።

በምእራባዊቷ የካናዳ ግዛት ስር ባለችው የብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዋና ከተማ ቫንኮበር ከ7-10ሺህ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን 34ኛ ዓመት ላይ ያለ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ በቫንኮበርECA] የሚባል ማህበር ያላቸው ቢሆንም ማህበሩ በየዓመቱ በጋ የኢትዮጵያውያን ቀን ተብሎ የሚያከብረውን ዓመታዊ ፌስቲቫል በአቶ ከበደ ሃይለማርያም ጥረት በ2010 እንደጀመረ እና ዘንድሮ በሓምሌ 15ቀን 2017 በድምቀት የተከበረው 8ኛ ግዜ እንደሆነ መረዳት ችያለሁ።

image

በዚህ በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ ከሀገራቸው ከተሰደዱም በሃላ በያሉበት እስቴትና ሀገር ሳይታክቱና ሳይሰላቹ የሀገራቸውን ማንነትን በመግለጽ ማህበረሰቡንም በማስተባበር እና በማቀራረብ የበኩላቸውን ስራና ድርሻ እያበረከቱ ያሉትን ግለሰቦች፣ተቋሞች እና ማህበረሰባዊ ማህበራትን ስራ በተከታታይ የማቅረቡና የማስተዋወቁን ስራዩን ዛሬ በቫንኮበራ የኢትዮጵያን ኮሚኒቲ ማህበርና ለ14ዓመታት በተለያየ የሃላፊነት ደረጃ በማህበሩ ውስጥ ያገለገለውን እና ዛሬም በተመሳሳይ ተግባር ላይ በተሰማራው አቶ ከበደ ሃይለማርያም እንቅስቃሴ ዙሪያ ያነጣጠረውን ጥንቅር እንደሚከተለው አቅርቤያለሁ።

**የአሰቡ ከበደ ሃይለማርያም ቀበሌ ታሪክ

ዛሬም ጭምር በአሰብ ያሉ ታክሲ ነጂዎች ከበደ ቀበሌ እያሉ ቢጠቀሙበትም የቀድሞው 03-04ተብሎ የሚጠራው ቀበሌ አቶ ከበደ ሃይለማርያም በሊ/መንበርነት ባገለገለበት 1980ዎቹ ውስጥ ነዋሪው በፍቃደኝነት በከበደ ሃይለ ማሪያም ቀበሌ ስም ቀይሮት እሰከ 1991የደርግ ስርዓት መፍረስ ድረስ መጠሪያ እንደነበር ይናገራል።

እንዴት የአንድ ከተማ ቀበሌ ስም በአንድ ግለሰብ በሆነው በአንተ ስም ሊሰየም ቻለ ? ምን የተለየ ስራ ብትሰራ ነው ማህበረሰቡ ቀበሌውን በአንተ ስም ለመሰየም የቻለው ለሚለው ጥያቄዪ አቶ ከበደ ሲመልስ “ቤቶቹ በአጠቃላይ በሳር የለበሱ እና የጎሰቀሉ ነበር። በሊቀመንበርነት እንደመረጡኝ ከቀበሌው ለመንግስት የምናስገባውን ማንኛውንም ገቢ ግብር ጭምር ለሁለት ዓመት አቆምኩና በገንዘቡ ቆርቆሮና አስቤስቶ በማስመጣት እንዲሰራ አደርኩኝ።መንግስትም የህዝቡን ገንዘብ ያለ አግባብ አባክነሃል በማለት ሲያስረኝ ህዝቡ ግልብጥ ብሎ በመውጣት የለም ከበደ ቤታችንን እና ኑሮዋችንን አሻሻለበት እንጂ ለራሱ ምንም ያደረገበት የለም ብሎ አስፈታኝ። ቀበሌውን ዜሮ ሶስት ዜሮ አራት የሚለውን ለውጠው ከበደ ሃይለማርያም ብለው ሰየሙት ” ሲል አቶ ከበደ ይናገራል።

19ኛ ዓመቱን በካናዳይቱ የቫንኮበር ከተማ ያከበረው የዘጠኝ ልጆች አባት እና የልጅ ልጆች አባት የሆነው አቶ ከበደ ሃይለማርያም የአንድ ወር ህጻን ልጅ ሳለ ወላጆቹ ወደ አሰብ በስራ በተዛወሩበት ወቅት አሰብ ሊገባ የቻለ ሲሆን እስከ 1991 ድረስ አድጎ ለወግ ማእረግ የበቃበትና በስራም ዘርፍ ያሳለፈበት ከተማ አሰብ እንደሆነች ነግሮኛል።

በ1952.ዓ.ም በብርዳማዋና ደጋማዋ ደብረ ሲና ከተማ የተወለደው አቶ ከበደ የአሰብን ቃጠሎ እንዴት እንዴት እንደተላመደው እግዜሩና ህይወት ይወቁለትና ወደ ካናዳ ከማቅናቱ በፊት ከ1991 እስከ 1999 ድረስ በኬኒያ ስደተኛ ሆኖ እንደኖረም ከንግግራችን መረዳት ችያለሁ።
በኬኒያ ስምንት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ካናዳ በመጓዝ ከእነ ሙሉ ቤተሰቡ በቫንኮበር ህይወትን ሀ-ብሎ የጀመረ ሲሆን በ8ኛ ወሩ ላይ በኬኒያ እንቅስቃሴውን በሚያውቁለት ኢትዮጵያውያን ተጠቁሞ ተዳክሞና ለመፈራረስ ተቃርቦ የነበረውን በቫንኮበር የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ማህበር እንዲመራ ይደረጋል።

የቫንኮበሩ የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ማህበር የተመሰረተው በ1983 ሲሆን ማህበሩ የእድሜውን ያህል አድጎና ደርጅቶ መገኘት ያልቻለበት ዋና ምክንያት የኢትዮጵያውያኑ የማህበሩን ጥቅም በአግባቡ ያለመረዳት፣የማህበሩ አባላት ቁጥር ማነስ፣ለማህበሩ መደራጀት ልባዊ ስራን እና ፍቃደኝነት ማህበሩን ለመምራት በሚመረጡት ኮሚቴዎች ዘንድ በአግባቡ አለመኖርና ብሎም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዘር ተኮር ፖሊሲ የፈጠረው ሁኔታ ከሚጠቀሱት ውስጥ በዋነኝነት የተጠቀሱ ናቸው ሲሉ አብዛኞቹ ያነጋገርካቸው ይናገራሉ።

ከተመሰረተ 13ዓመት የሆነውን ማህበር እንድመራ ሲሰጡኝ ከአባላት መዋጮ ከሚሰበሰበው 300$ዶላር ነበር የሰጡኝ የሚለው አቶ ከበደ ሃይለማርያም ለ14ዓመት በማህበሩ ሊ/መንበርነት፣ም/ል ሊቀመንበርነትና ብሎም በማህበሩ ህዝብ ክፍል ግንኙነት ለ14ዓመታት አገልግሎ በ2014 ሃላፊነቱን ለአዲስ ተመራጮች ሲያስረክብ ማህበሩ አቶ ከበደ ሃይለማርያምን በቫንኮበር የኢትዮጵያውያን አምባሳደር ብሎ በደብዳቤ እንደገለጸለት አጫውቶኛል።

በአቶ ከበደ በቫንኮበር የኢትዮጵያን ኮሚኒቲ አምባሳደርነት ስም የረዥም ዘመን የቅርብ ወዳጁና በኮሚኒቲው ውስጥ ባልደረባ የሆነው አቶ ኦሪዮን መንግስቴ ይስማማበታል። አባባሉን ማጠናከሪያ እንዲህ ሲል ይናገራል..” ከበደን የማያውቅ ማንም የለም። እሱም የማይገባበትና የማያውቀው ስውና ስፍራ የለም። ቅን፣ደፋርና ፈጣን ነው።የተጎዳና እርዳታ የሚያስፈልገው ኢትዮጵያዊ አይቶ አያልፍም። የብዙ ኢትዮጵያውያንን አስከሬን እንዳይቃጠል አድኗል። በቅርቡ የሆነ ቤተሰብ ከኦሮሞ ኮሚኒቲ አስጨናቂ ችግር ይገጥማቸዋል።ቤተሰቡ ወደ ኢትዮጵያን ኮሚኒቲ መቅረብ የሚፈልጉ ስላልነበረ ይቸገራሉ። ሆኖም ከበደን ቀርበው ይገልጹለታል። እጅግ አስቸጋሪ ሰፈር ነበር የሚኖሩት። ከቤተሰቡ አንድ ሰው ሞቶ ነበር ለመቀበሪያ ተቸግረው የፈለጉት። ሁላችንም አየን እናም አዘንን። የሞተውን በአግባቡ ከቀበርን በኋላ ከበደ ከከንቲባው ጽ/ቤት ባለስልጣናቱን ወስዶ የሚኖሩበትን በማሳየት እንዴት ይህ ሁሉ ቤተሰብ እናንተ ባላችሁበት እንደዚህ ዓይነት ሰፈርና ቤት ውስጥ ይኖራል ብሎ ጠየቃቸው። በማግስቱም ባለስልጣናቱ ያንን ቤተሰብ ከመጥፎው ሰፈርና መኖሪያ አውጥተው ባለ አምስት ክፍል ቤት በመስጠት እንዲኖሩበት ፈቀዱላቸው።” ይልና አቶ ኦሪዮን “ከበደ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይል በተፈለገበትና ኢትዮጵያዊ ባለበት ቀድሞ የሚገኝ ሰው ነው። አዳዲስ መጪዎችና ቤተሰባቸውን ያላመጡ ኢትዮጵያውያን የሚጠይቁት ከበደን ነው” ሲል ይናገራል።

የኢትዮጵያን ማህበረሰብ ኮሚኒቲ ማህበር ዋና ዓላማውን ኢትዮጵያዊነትን እና ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጠናከር ከዘር፣ከሃይማኖት ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ነጻ ሆኖ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አገልግሎቱን በእኩልነት ለመስጠት የተቋቋመ ማህበር ነው። አቶ ከበደ የሊ/መንበርነቱን ስፍራ ከ300ብር ካፒታል ጋር ከተሰጠው በኋላ በ2014 ሲያስረክብ ከ20ሺህ$ በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ፣የአባላቱ ቁጥርም አድጎ እና በ2010 በአቶ ከበደ ፍቃድ አውጪነት ዓመታዊው የኢትዮጵያውያን የበጋ ፌስቲቫል ተደራጅቶ እንደሆነ አቶ ኦሪዮን ገልጾልኛል።

ታዲያ ይህ ሰልፍለስ ጥረቱ በወገኖቹ ዘንድ ብቻ ተወስኖ የቀረ የማይመስልበት ምክንያት አቶ ከበደ በከናዳ የንግስት ኤሊሳቤት 2ኛ [Ethiopian Human rights advocate ato Kebede Hailemariam Abate, awarded Queen Elizabeth II Diamond Jubilee Medal here in Vancouver, Canada]የክብር ሜዳሊያ በበጎ አድራጎትና ተግባራቱ እውቅና ሽልማትን በ2013 ላይ ተሸላሚ በመሆን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሆኑ ነው። ከኢትዮጵያዊነቱ ሌላ በካናዳዊነቱ አቶ ከበደ በካናዳ ፖሊስ ሃይል ውስጥ በፍቃደኝነት ያገለገለ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም የቫንኮበር ገዢ ከሆነው ተቃዋሚው NDP አባል የሆነ ሲሆን በAfrican Dissent Canadian Association, እና በETHIO-Canadian Refugee Association ውስጥ በቦርድ ሰብሳቢነት እያገለገለ ያለ ሲሆን “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አዲስ መጪና የቆየም ቤተሰቤን ወደ ካናዳ ለማምጣት እፈልጋለሁ ካለ በነጻ የአገልግሎት ተግባር እንፈጽማለን ያነጋግሩኝ ” ሲል ተናግራል።

image

አቶ ከበደ ሃይለማርያም የንግስቲቱን የክብር ሜዳላይ ሽልማት ያስጠው በስነ ስርዓቱ ላይ እንደተገለጸው በፍቃደኝነት እያደረገ ላለው ማህበረሰቡን ለሚጠቅም ስራው እውቅና መስጫ ተደርጎ ሲሆን በተለይም በ2000ዓ.ም አቶ ኦሪዮን መንግስቴም ተሳታፊ በሆነበት በኢትዮጵያ በድርቅ ለተጎዱት ወገኖቻችን በቫንኮበር ያሉትን ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ክ40ሺህ$ ብር በላይ በቀይ መስቀል በኩል ስንዴ ተገዝቶ እንዲደርስ ያደረጉት ተግባር ተጠቅሶ ይገኛል።

ይህ የንግስቲቱ የክብር ሜዳሊያ ተሸላሚነቱ አቶ ከበደን በማንኛውም የካናዳ ብሔራዊ ክብረ በዓላት እለት በየዝግጅቱ በክብር እንግድነት እንዲጠራ አድርጎታል። በቅርቡም ካናዳ 150ኛ ዓመቷን ልዩ ክብረ በዓል ስታከብር በቫንኮበር የክብር እንግዳ ተደርጎ የበዓሉን ኬክ የቆረሰው ኢትዮጵያዊው አቶ ከበደ ሃይለ ማርያም ሲሆን ይህ ያለው ግንኙነትም ለማህበሩ መጠናከር፣ቦታና መሰብሰቢያ የማግኘት ትልቁን ድጋፍ አድርጓል ሲል ኦሪዮን ይናገራል።

“በቫንኮበር ያሉት ከንቲባ፣ፖለቲከኞችና በኦቶዋ ያሉት የፓርላማ አባላት ጋር ጥብቅ ግንኙነት አለው።የብርቱካን ሚደቅሳን እና የአትሌት ለሊሳ ፈይሳን ጉዳይ ባነሳልህ ጠ/ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን መንግስት የፖለቲካ እስረኛዋን ብርቱካን ሚደቅሳን መፍታት አለበት ብለው በፓርላማ ደረጃ እንዲናገሩ የቻሉትና በለሊሳ ፈይሳ ጉዳይ ካናዳ ለአትሌቱና ለቤተሰቡ ለመቀበል ዝግጁ ናት ብለው ፍቃደኝነታቸውን የገለጹት ከበደ ባለው የግንኙነት መስመር ተጠቅመን በጻፍንላቸው ደብዳቤ ምክንያት ነው” ሲል አቶ ኦሪዮን ይናገራል።

image
እንደ አቶ ኦሪዮን እና አቶ ከበደ አባባል አትሌት ለሊሳ ፈይሳ በብራዚል ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንዳይችል ያደረገውን ቅዋሜ ከገለጸ በኋላ በቫንኮበር ያሉት የኢትዮጵያን ኮሚኒቲ የካናዳ መንግስት የአትሌቱ ህይወት እና ቤተሰቡ በአደጋ ላይ ስላለ የካናዳ መንግስት ጥገኝነት እንዲሰጠው ብለው ለጠ/ሚሩ ደብዳቤ የጻፉ ሲሆን ጠ/ሚ/ሩም የዘገዩ ቢሆንም እሺታቸውን መልስ የላኩላቸው ሲሆን በወቅቱ ግን አትሌቱ በአሜሪካን መንግስት ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ ወደ አሜሪካን ሊያመራ ቻለ እንጂ ወደ ካናዳ እንዲጓዝ የሚያስችለውን ሁኔታ እንዳመቻቹለት ነው መረዳት የቻልኩት።

image

የዘጠኝ ልጆቹ እናት ወ/ሮ አለምጸሃይ ጸሀይ በአቶ ከበደ ህይወት ውስጥ ብርቱ የድጋፍ ሚናን ከጓደኛው አቶ ኦሪዮን በኩል ማወቅ የቻልኩ ሲሆን እሱም ቢሆን በባለቤቱ መኩራቱን ከመግለጽ ወደኋላ የማይለው አቶ ከበደ በኬኒያ የስምንት ዓመት ቆይታው በJRS በጎ አድራጊ ድርጅት ጋር በደቡብ ሱዳን፣በሩዋንዳ፣በኮንጎና በዮጋንዳ እየተዘዋወረ ሲሰራ እንደነበር ተናግሯል። የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ጋር የቅርብ ግንኙነት ትውውቅ ያለው ሲሆን በኬኒያ ቆይታውም ከሀገሪቱ ታላላቅ ባለስልጣናት ጋር መተዋወቁን የሚገልጸው ዛሬም በቫንኮበር በኢትዮጵያዊነትና በኢትዮጵያዊ አንድነት ዙሪያ በማስተባበር በመተባበርና ብሎም ያለድካምና ስልችት በመንቀሳቀስ የሚታውቅ ሰው ሆናል።