የሳኡዲ ቀነ ገደብ ተገባዷል፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ህይወት ለአደጋ እንደተጋለጠ ነው ተባለ

አባይ ሚዲያ ዜና
በወንድወሰን ተክሉ

የመጀመሪያው 90 ቀን የመውጫ ቀነ-ገደብ ከተጠናቀቀ በኋላ በተጨማሪ የተሰጠው የአንድ ወር ግዜ የተጠናቀቀ ቢሆንም እስከ ዛሬ ድረሰ ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ66 ሺህ እንደማይበልጥና በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት ህይወት በአደጋ ላይ መውደቁ ተገለጸ።

በሳኡዲ ዓረቢያ መንግስት በሁለት ዙር የተሰጠው አጠቃላይ 120 የምህረት ቀን በተገባደደበት በአሁኑ ሰዓት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ከተመዘገቡት 135 ሺህ በላይ ውስጥ ወደ 66 ሺህ የሚጠጉት መመለስ መቻላቸውን ከኢትዮጵያ መንግስት መግለጫ መረዳት የተቻለ ሲሆን 70 ሺህ የሚጠጉት ተመዝጋቢዎች ግን ሳኡዲን ሳይለቁ ቀነ ገደቡ እንደተጠናቀቀባቸው ነው መረዳት የተቻለው።

በሳኡዲ ዓረቢያ የተለያዩ ግዛቶች ወደ 400 ሺህ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ የሚታወቅ ሲሆን ከጂዳ፣ ሪያድ እና ጂዛን ግዛት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በስልክ በደረሰን መረጃ መሰረት አብዛኞቹ ወደ ሀገራቸው ከመመለስ ይልቅ በሳኡዲ መንግስት የሚደርስባቸውን ቅጣት ለመቀበል አሊያም ወደ የመን ለመሰደድ መወሰናቸውን ነው መረዳት የቻልነው።

የመን በእርሰበርስ ጦርነት እና በአስከፊ ርሃብ ጥቃት ስር ያለች ሀገር ሆና ሳለ ኢትዮጵያውያኑ ግን ወደ ሀገራቸው ከመመለስ ይልቅ ወደ እዚህች ሀገር ለመጓዝ መወሰናቸው ምን ያህል የሀገራቸው ሁኔታ እንዳስፈራቸው መረዳት ይቻላል ሲሉ የሰብዓዊ መብት ተማጓቾች ይናገራሉ።

የሳኡዲ መንግስት የስራ ፍቃድ የሌለው ማንኛውም የውጭ ዜጋ ሀገሪቱን በታወጀለት ግዜ ገደብ ለቆ ካልወጣ መንግስት የሃይል እርምጃን በመጠቀም በግድ እያሰረ እንደሚመልስ ያስጠነቀቀ ሲሆን ለሚደርሰውም ማንኛውም ጉዳት ተጠያቂ እንደማይሆን መግለጹ አይዘነጋም።