በአምቦ ቄሮዎች እርምጃ ወሰዱ፣ ምእራብ ኦሮሚያ በአድማ እንደተመታች ነው

አባይ ሚዲያ ዜና
በወንድወሰን ተክሉ

በምእራብ ኦሮሚያ አምቦ ከተማ ማምሻውን በተነሳ ህዝባዊ አመጽ ንብረትነቱ የመንግስት የሆነ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መኪና በቄሮዎቹ በእሳት የጋየ ሲሆን ንብረትነቱ የህወሃት የሆነው ሰላም አውቶቢስ [ሰላም ባስ] በደረሰበት የድንጋይ ጥቃት ከጥቅም ውጪ እንደህነ ከአምቦ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ለህወሃት መራሹ ሌባ መንግስት ግብር አንገብርም፣ የተመደበብን የማይገባ ግብር ነው እና የመሳሳሉትን መፈክሮች ይዘው ወደ አውራ መንገድ የወጡት ቄሮዎቹ በከተማዋ የሰፈረው የፌዴራል ሰራዊት እና የፖሊስ ሰራዊት ሳይበግራቸው ቁጣቸውን እና ተቃውሞዋቸውን በመንግስታዊና በፓርቲ ንብረቶች ላይ በማድረግ አውድመዋል።

ከተማዋ ዳግም በአግዓዚ ሰራዊት ብትጥለቀለቅም ነጋዴውም ህብረተሰብ ተቋሙን በመዝጋት አድማውን ተቀላቅሏል።

በጊንጪ ትናንት አራት ባለስልጣናት ከስራ የተባረሩ ሲሆን ህዝቡ ግን በተጠራበት ስብሰባ ላይ ሳይሳተፍ ጥሎ ተመልሷል።

በዓለም ገና ከተማ የስራ ማቆም አድማው ተጠናክሮ የቀጠለ በመሆኑ የትራንስፖርት እጥረት ከፍተኛ ችግር ሲፈጥር ተስተውሏል። በጅማ ያለውን የስራ ማቆም አድማ ለመቀልበስ በተጠራው ስብሰባ ላይ ህዝብ መገኘት ባለመፍቀዱ የታሰበለትን የማቀዝቀዝ ተግባር መፈጸም አልተለም።

በምስራቅ ኦሮሚያ ደደር ከተማ ለሶስተኛ ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የሰነበተው የስራ ማቆም አድማ እንደቀጠለ ሲሆን የአግዓዚ ሰራዊት አድማውን ለማስቆም በወሰደው የአፈሳ ዘመቻ በርካታ ለፍቶ አደርና በረንዳ አዳሪ ወጣቶች ታፍሰው እንደታሰሩ ለማወቅ ተችሏል።

ኢ-ፍትሃዊ የሆነውን የግብር ተመን በመቃወም በኦሮሚያ የፈነዳው ህዝባዊ ተቃውሞ ከአንድ ስፍራ ወደ አንድ ስፍራ እየተቀጣጠለ ሲካሄድ ሁለተኛ ሳምንቱን የያዘ ቢሆንም በመንግስት በኩል አንዳችም የማሻሻያ እርምጃ እንዳልተሰጠ ይታወቃል።