ላዩን በኢትዮጵያዊነት ቅብ የሸፈነው የሮማው የስፖርትና ባህል ፌስቲቫል (ካሳይሁን በቃሉ)

0

ዘንድሮ ሮማ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘውን 15ኛውን የአውሮፓ ስፖርትና ባህል ፌስቲቫል አስመልክቶ በወያኔ ስለመጠለፉ ሊስተባበሉ የማይችሉ በርካታ ማስረጃዎች ከቀረቡበት በኋላ በከፍተኛ ውግዘት ውስጥ ሆኖ እስከዛሬ ተጉዟል። ፌዴሬሽኑ የችግሩን ጥልቀትና ውሎ አድሮም ሊያስከትል የሚችለውን መከፋፈል ቸል በማለት ለጊዜያዊ ጥቅምና ለዘንድሮው ብቻ ለመዳን በማሰብ ነገሮችን ሸፋፍኖ ህብረተሰቡን የማሞኘት ዓይነት ተግባራትን ሲያከናውን ታዝበናል። የሚሰማን አላገኘንም እንጂ እንደአቅማችን ምክር ለመሰንዘርም ሞክራናል።

በግልጽ የተነገሩት ችግሮች ሁለት ናቸው። አንዱ በተለያዩ ሀገራት ያሉ ክለቦች የዝግጅት ፈቃድ ከማግኘት አንስቶ የተሳትፎ ሁኔታን እንዲሁም በፌዴሬሽኑ ውስጥ ግልጽ አሰራር ያለመኖሩንና ቅሬታ የሚስተናገድበት አግባብ መታጣቱን አስመልክቶ የተነሱት ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ሲሆን ሁለተኛውና ከበድ ያለው ችግር ደግሞ የዘንድሮው ዝግጅት ገና ከጅምሩ ሮማ እንዲደረግ የተወሰነበት ድብቅ አሰራርና ዝግጅቱን ለማካሄድ የሚያስችለው ገንዘብና ክንውኑን የሚቆጣጠሩት አካላት ከኢትዮጵያ መሆናቸውን መነሻ በማድረግ የሮማው ዝግጅት በወያኔ መጠለፉን በርካታ ማስረጃዎች ቀርበውበት ብዙ የተባለበት ነው። እንግዲህ ችግሮቹን ካየናቸው ፌዴሬሽኑም ችግሮቹን ከመሰረታቸው የመፍታት አርቆ አሳቢነት ቢኖረው ኖሮ ትኩረቱን በተነሱት ጥያቄዎች ላይ በማድረግ ዘላቂ መፍትሄ ለመፈለግ ሲጥር በታየ ነበር። ጭራሹኑ ከዚህ በተቃራኒ በመሄድ እንደውም ችግሮቹን በሚያባብሱ ወይንም በሚያድበሰብሱ ጉዳዮች ላይ ሲውተረተር ታይቷል።

ክለቦች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች በቂ ንግግር አድርጎ ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ ከመስራት ይልቅ ማገድና አንዳንዴም ክለቦችን ለሁለት በመሰንጠቅ ለሚፈልጉት አካል ብቻ እውቅና መስጠትን የመሳሰሉ ወያኔያዊ ተግባራት በስፋት የተለመዱ ሆነዋል። እዚህ ላይ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። በጀርመን የኢትዮ በርሊን ቡድን አንዳንድ መሰረታዊ ጥያቄዎችን እያነሳ ፌዴሬሽኑን ሲጠይቅ በሀሳብ ሙግት ከመስማማት ይልቅ ክለቡን ለሁለት በመሰንጠቅ ዘበርሊን የተሰኘ ቡድን በመፍጠር ለነባሩ ክለብ እውቅና በመንፈግ ለአዲሱ ክለብ ፈቃድ የሰጠበትን ሁኔታ መጥቀስ ይቻላል። ይህ ማለት ወያኔ ቅንጅትን ከነባሩ አመራር ነጥቆ ለአየለ ጫሚሶ እንደሰጠው አይነት መሆኑ ነው። እንግዲህ እንደዚህ ዓይነት ከፋፋይ ተግባራትን እየፈጸመ ያለ ፌዴሬሽን ነው ኢትዮጵያዊያንን ማሰባሰብ ዓላማዬ ነው የሚለው።

ከላይ በተጠቀሱት ዓይነት ጭቃ ውስጥ እየቦካ የከረመው ፌዴሬሽን የዘንድሮውን የሮማ ፌስቲቫል ጠቅልሎ ለወያኔ ካስረከበ በኋላ በሂደቱ የተነሱትን በወያኔ የመጠለፍ ጥያቄዎችንም ለመመለስ የሄደበት መንገድ ያው ወያኔያዊ ነበር ማለት ይቻላል። የተለያዩ ጉዳዩ ያገባናል ያሉ አካላት ሀሳባቸውን በመገናኛ ብዙሀን ስለገለጹ ሚዲያዎችን መስደብና ሀሳባቸውን የሚገልጹትን ወገኖች ተቃዋሚዎች በሚል ለማሸማቀቅ የመሞከር ምግለጫዎች ሲሰጡ ሰምተናል። የሮማው ዝግጅት አዘጋጆች ማንነትና የፌስቲቫሉ በወያኔ መጠለፍ አጀንዳ እያየለ ሲመጣም ዝግጅቱ ወያኔ ወያኔ እንዳይሸት የመቀባባት ስራ መስራትም ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነበር። በብዙ ትርምስ ውስጥ አልፎ ለፌስቲቫሉ የተቆረጠው ቀን ደርሶ ዝግጅቱ ሲጀመርም ጊቢውን በንጹሁ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ከማስዋብ አንስቶ የቴዎድሮስ ካሳሁንን ኢትዮጵያ ሙዚቃ በመደጋገም ወያኔነትን በኢትዮጵያዊነት የመቀባት ስራ በሰፊው ተሰርቶ ታይቷል። እዚህ ላይ ለቅብ ተብሎ ከፍ ያለው ኢትዮጵያዊነትም ቢሆን ስለነጻነት የበኩላቸውን ለሚያደርጉ ወገኖች ትልቅ ድል ነው። ምክንያቱም ወያኔ ህብረተሰቡ ያለበት ለመድረስ ራሱን ደብቆ ካልሆነ በስተቀር ወያኔ ነኝ ብሎ አደባባይ መቆም እንደማይችል ያረጋገጠ ተግባር ነውና። እዚህ ላይ የዘንድሮው ዝግጅት በወያኔ የመጠለፉን ዜና የሰማው ሀገር ወዳድ ህዝብም ኢትዮጵያዊነት እንዲደምቅ እያሳየ ያለው እልህ የተሞላበት ወኔም ሳይጠቀስ አይታለፍም።

እንግዲህ ቀደም ሲል ዝግጅቱን እየተቆጣጠሩ ያሉት፣ ቦታዎችን የደለደሉት፣ ገንዘብ የመደቡትና የሚሰበስቡት የወያኔ ልዑካን እንደሆኑ በማስረጃ ተደግፎ ተገልጿ። እነዚህ ዝግጅቱን የሚቆጣጠሩት የወያኔ ሰዎች ዛሬም ስራውን እየሰሩ ነው። በጊቢው ውስጥ ያሉት ድንኳኖች የተሰጡት ለስርዓቱ ሰዎችና የቅርብ ባለሟሎች ነው። ለምሳሌ በምግብ ድንኳን አካባቢ ለምግብ ስራ ከተያዙት ውስጥ ከወያኔ ሰዎች በዙሪያቸው ካሉ አሸርጋጆች ወጪ ለአንድ ሰውም የተሰጠበት እውነታ የለም። ለዚህም ነው ወያኔ እራሱን በኢትዮጵያዊነት ሸፍኖ እየነገደ ነው የምንለው። ከዚያም ባለፈ ፌዴሬሽኑ ዝግጅቱ በወያኔ ተጠልፏል በሚል የቀረበበትን ወቀሳ ለመደበቂያነትና ከወያኔ ነጻ የሆነ ፌዴሬሽን ያስፈልገናል የሚሉ ወገኖች ተራ አሉባልታ ያባዛሉ ለማለት ኢትዮጵያዊነትንና ሰንደቅ አላማን መደበቂያና ማደናገሪያ እያደረገ ይገኛል። እውነቱ ግን ከኢትዮጵያዊነትና ከሰንደቅ አላማው ጀርባ ሮማ ላይ ንግዱን የሚያካሄደው ወያኔ ነው። ኢትዮጵያዊነትና ሰንደቅ ዓላማችን የገዳዮች መነገጃ ሲሆን ደግሞ ያመናል። ያ አሮጊቷን በልጇ አስክሬን ላይ አስቀምጦ የደበደበ ስርዓት፣ የህጻናትን፣ የወጣቶችን፣ የአረጋዊያንን ደም ያፈሰሰ፣ የሀገሪቱን ብርቅ ልጆች እስር ቤት ውስጥ አጉሮ ያኮላሸ፣ የየእለቱ የህዝባችን ኑሮ የሰቆቃና የዋይታ እንዲሆን ያደረገው ወያኔ በስደት ባለንበት ደጃችን መጥቶ ሲነግድ ገንዘቤን አልሰጥም ማለት ፍትሀዊ ብቻ ሳይሆን በስርዓቱ ጥቃት ስር ላሉ ወገኖችዎም አለኝታ መሆን ነው።