በሙስና የበሰበሰ አገዛዝ ሙስናን ሊታገል አይችልም!!!

0

መፍትሔው ሙስናን መሰባሰቢያ አድርጎ የተመሰረተውን ህወሃት/ኢህዴግን ከመሰረቱ መታገልና በሀዝባዊ አስተዳደር መተካት ብቻ ነው!!!
(በሰማያዊ ብሔራዊ ሸንጎ የተሰጠ መግለጫ)

ህወሃት/ኢህአዴግ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከባድ ፍጥነት አንቅሮ እየተፋውና ከላዩ ላይ ለማውረድ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ውጥረት ሲበዛበት የተለያዩ ሰሞነኛ ማደናገሪያዎችን ይዞ ብቅ ማለት ዋነኛ ባህሪው መሆኑን አለምም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቀው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በዚህ ማደናገሪያ ባህሪው የሚታወቀው ህወሃት/ኢህአዴግ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተቀሰቀሰበትን ውጥረት ለማርገብ ‘ፀረ ሙስና ትግል’ የምትል ወቅታዊ ማደናገሪያ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡

በመሰረቱ ህወሃት/ኢህአዴግ ዋናው የመሰባሰቢያ መሰረቱ ጥቅም ወይም ሙስና ነው፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግና ሙስና የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ ካለ ሙስና አለ ሙስና ከሌለ ህወሃት/ኢህአዴግ የለም፡፡ ስለዚህ ድርጅቱ የቆመበትንና የመሰባሰቢያ ምሰሶው የሆነውን ሙስናን ለመታገል እና ለማጥፋት የተፈጥሮ ባህሪው አይፈቅድለትም፡፡ በመሆኑም ሙስናን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ሙስናን መሰባሰቢያ አድርጎ የተመሰረተውን ህወሃት/ኢህዴግን ከመሰረቱ መታገልና ከስልጣን ማውረድ ያስፈልጋል፡፡
ይህንን ከላይ የተገለፀውን መሰረታዊ ሀቅ በምሳሌ ለማሳየት አገዛዙ የፀረ ሙስና ትግል በሚል ማደናገሪያ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ፣ የቀድሞውን መከላከያ ሚኒስትር አቶ ሰዬ አብርሃ፣የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሃላፊዎች አቶ ገብረ ዋህድ እና አቶ መላኩ ፋንታ በተለያየ ጊዜ በሙስና ተጠርጥረው ለፍርድ ቀረቡ ሲባል ሰምተናል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለው ነገር ከተራ ሰሞነኛ የፖለቲካ ማደናገሪያነት አልፎ እታገለዋለሁ በሚለው ሙስና ላይ ውጤት ሊያመጣ ቀርቶ በይዘትና በስፋት ጨምሮ ለጆሮም ሆነ ለአምሮ በሚከብድ ሁኔታ ሙስና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ፈጣሪውን ስርዓቱን እየበላ አገዛዙ የተፈጥሮ ሞቱን ለመሞት እየተቃረበ ነው፡፡

አገዛዙ አሁን ላይ ያለበትን የመበስበስ ደረጃ ከታሪክ ምሳሌ ጋር በንፅፅር ለማሳየት የአፄ ኃይለ ስላሴ አገዛዝ በአራቱም አቅጣጫ ህዝባዊ ተቃውሞ ሲበረታበት እና መያዣ መጨበጫ ሲያጣ ሙስናንና የአስተዳደር ብልሹነትን የሚያጣራ በእነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም የሚመራ መርማሪ ኮሚሲዮን አቋቁሞ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በዚህ መርማሪ ኮሚሲዮን የስራ ሪፖርት ላይ አዳምጦ እርምጃ ለመውሰድ እንኳ ጊዜ ሳያገኝ በስብሶ እንደተገረሰሰ ታሪክ የሚያውቀው ሃቅ ነው፡፡ ታሪክ እራሱን ይደግማል እንዲሉ ህወሃት/ኢህአዴግ በተለያዩ ውስብስብ ችግሮች ወደ ሞት አፋፍ እየተቃረበ ባለበት በአሁኑ ወቅት በፌደራል ጠቅላይ ዓቃቢ ህግና በፌደራል ፖሊስ ልዩ መዋቅር አቋቁሜ ፀረ ሙስና ትግል ዘመቻ አውጃለሁ ይለናል፡፡ ይህ በግልፅ የሚያሳየን አገዛዙ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉት ውስብስብ የፖለቲካ፣የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግሮች መፍትሔ መስጠት የማይችልበት የመጨረሻ ደረጃ ላይ መሆኑን ነው፡፡
በመሰረቱ ሙስናን እንደ ወረርሽኝ እና የተፈጥሮ አደጋ በዘመቻና በሰሞነኛ ግርግር መታገል አይቻልም፡፡ ሙስናን በመሰረታዊነት ለመታገል፡-
1. ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ የሆነ ሲቪል ሰርቪስ መኖር አለበት
2. የመንግስትን አሰራር በድፍረት የሚተቹ ነፃ የመገኛኛ ብዙሃን መቋቋም አለበት
3. ህዝብ ለመብቱ እንዲቆም የሚያስተምሩ ሲቪክ ማህበራት መኖር አለባቸው
4. ህዝብ የሀገሩና የስልጣን ባለቤት እንዲሆንና የፈለገውን መሾምና ያልፈለገውን መሻር የሚችልበት ስርዓት መመስረት አለበት፤
5. ጠንካራ የብዙሃን ፓርቲ ዴሞክራሲ ሲፈጠርና የመንግስት አሰራር ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው ስርዓት መዘርጋት አለበት፤
6. ጠንካራ ብሔራዊ ስሜትና የሀገር ፍቅር በመገንባት ለሀገርና ለህዝብ አስተዋጾ ማድረግ የሚያኮራ ተግባር መሆኑን የሚገነዘብና የሐገርና የወገንን አዳራ የሚያከብር ዜጋ ሲፈጠር ብቻ ነው፡፡
ከላይ በተጠቀሱት መመዘኛዎች መሰረት ህወሃት/ኢህአዴግ ተፈትኖ የወደቀ ስለሆነ ከዚህ አገዛዝ ሀቀኛ የፀረ ሙስና ትግል ውጤት ማሰብ ከእባብ እንቁላል እርግብ እንደመጠበቅ ነው፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሃት/ኢህአዴግ በየጊዜው በሚፈጥራቸው ሰሞነኛ ማደናገሪያዎች ሳይዘናጋ የችግሮች ሁሉ ምንጭ የሆነውን አገዛዝ ከመሰረቱ በመታገል በኢትዮጵያ ነፃነትና ዴሞክራሲ ለማስፈን የጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ሐምሌ 23 ቀን 2009 ዓ.ም
አዲስ አበባ