የሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን ሲያገለግል የነበረው አሊ ሱሌማን የባለሥልጣናትን የሙስና ፋይል ለሃለማሪያም ደሳለኝ በማቀበል በአምባሳደርነት ሹመት ከሃገር ሊወጣ እንደሆነ ታወቀ

0

የትንሳኤ ሬዲዮ በደረሰው መረጃ  መሠረት የሥነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን  ኮሚሽነር ሆኖ የህወሃትን አገዛዝ ሲያገለግል የኖረው አሊ ሱሌማን በአምባሳደርነት ሥልጣን ከመሾሙ በፊት በእጁ የሚገኘውን የባለሥልጣናት የሙስና ወንጀል ዝርዝር ፋይል ለሃይለማሪያም ደሳለኝ አስረክቦአል።

የቀድሞው የህወሃት ቁንጮ መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት ከተለየ ወዲህ አሊ ሰሌማን ለየትኛውም የአገዛዙ ባለሥልጣን ኮሚሺኑ የደረሰበትን የባለሥልጣናት የሙስና ፋይል ሠጥቶ እንደማያውቅ መረጃው ያመለክታል። ህወሃት ውስጥ በተፈጠረው ክፍፍልና አገሪቱን እየናጠ ባለው ህዝባዊ ተቃውሞ የአገዛዙ ዕድሜ አጭር መሆኑን ያሸተተው አሊ ሱሌማን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሥራው ላይ ደስተኛ እንዳልነበረና ሥራውን ለቆ ከአገር ለመውጣት ዕቅድ እንደነበረው ለግለሰቡ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ይናገራሉ።

ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ያላቸውን የሃብት መጠን ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ ሃላፊነት ተሰጥቶት የነበረው የሙስና ኮሚሽን መለስ ዜናዊ በሞት ከመለየቱ በፊት ያሰባሰባቸውን የባለሥልጣናት የሃብት መጠን መረጃ እስከ ዛሬ ድረስ ይፋ ሳያደርግ እንደቆየ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከሶስት አመት በፊት ከአሊ ሱሌማን ጋር አካሂዶት በነበረው ቃለመጠይቅ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ሃብት መጠን ለምን ይፋ እንዳልተደረገ ጠይቆት የሰጠው መልስ የግለሰቦችን የግል ህይወት መረጃ ይፋ ማድረግ ተገቢ እይደለም የሚል እንደነበር  ይታወሳል። አሊ ሱሌማን ድፍረትና ግልጽ አቋም የሌለው አድርባይ እንደሆነ የሥራ ባልደረቦቹ ይናገራሉ።

አሊ ሱሌማን ለሃይለማሪያም ደሳለኝ አሁን ባስረከበው  የሙስና ዝርዝር ውስጥ የእያንዳንዱን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት  ሃብት ዝርዝር የያዘ ሠነድ እንደሚገኝ እና ሠነዱን ከማስረከቡ በፊት በሥራ ሃላፊነት ከአገር ውጪ እንደሚመደብ ቃል ተገብቶለት እንደሆነ ለትንሳኤ የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

የህወሃት አገዛዝ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በተለያየ ሃላፊነቶች ሲያገለግሉት የነበሩ 12 ግለሰቦችን በአምባሳደርነት ሥልጣን ሲሾም አሊ ሱሌማን አንዱ እንደሆነ መገለጹ ይታወቃል። ህወሃት የሾማቸው12ቱ አምባሳደሮች በየትኛዎቹ አገሮች እንደተመደቡ እስክ ዛሬ አልተገለጸም።