ከሰሞነኛው ጉዳይ ጋር በተያያዘ የህወሓት ባለስልጣናት አለመግባባት ውስጥ መሆናቸውን ምንጮች ጠቆሙ

0

ባለፈው ሳምንት በሙስና ለእስር የተዳረጉ ሰዎችን አስመልክቶ እስሩ፣ የእስሩ ሒደት እና የታሰሩት ሰዎች ጉዳይ የህወሓት ባለስልጣናትን እያነታረከ ይገኛል፡፡ እስሩ በህብረተሰቡ ዘንድ ምንም ዓይነት ቦታ እንዳልተሰጠው በመግለጽ፣ ቢያንስ አንድ ወይም ሁለት ከፍተኛ የመንግስት አመራር መታሰር እንደነበረበት እየገለጸ የሚገኘው አንደኛው የህወሓት ቡድን፣ ከሌላኛው የህወሓት ቡድን ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡

በዚህ ሰዓት አንድ ወይም ሁለት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ማሰር፣ ስርዓቱን ማናጋት እንደሆነ የሚገልጸው ሌላኛው የህወሓት ቡድን በበኩሉ፣ አሁን በተያዙት ሰዎች እናዝግም የሚል አመለካከት መያዙን የመረጃ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በፊት ህወሓት አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን በሙስና ለማሰር ወይም ከስልጣን ለማንሳት ሲፈልግ የመጀመሪያ መስዋዕት የሚያደርገው፣ ብአዴንን አልያም ኦህዴድን መምታት ነው፡፡ ቀጥሎም ከሁለቱ አንዱ ወይም ከሁለቱም ፓርቲዎች በሙስና ስም አልያም በብቃት ማነስ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲነሱ ሲደረግ ነበር፡፡ ሆኖም አሁን ባለው የህወሓት መሰረታዊ የፖለቲካ አቋም፣ እንደከዚህ ቀደሙ ኦህዴድን አልያም ብአዴንን ለመምታት መሞከር የህወሓትን የበላይነት ማረጋገጥ ነው ተብሎ፣ የሙስና እርምጃው በትናንሽ የስራ ኃላፊዎች ላይ እንዲያተኩር ተደርጓል፡፡ ሆኖም እንደ አማራጭ ተደርጎ የተሔደበት መንገድ፣ ብዙም የፖለቲካ ትርፍ አለማምጣቱን የተመለከተው አንደኛው የህወሓት ቡድን፣ ትናንሽ የስራ ኃላፊዎች እንዲታሰሩ ትዕዛዝ ከሰጠው ሌላኛው የህወሓት ቡድን ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብቷል፡፡

የሁለቱን ዝሆኖች አለመግባባት ዳር ሆነው እየተመለከቱ የሚገኙት ብአዴን እና ኦህዴድ፣ በቀጣይ ምን ዓይነት ቁጣ ሊወርድባቸው እንደሚችል የታወቀ ነገር የለም፡፡

መንግሰት ከዚህ በኋላ እንዳስፈላጊነቱ በቁጥጥር ስር ሊውሉ የሚችሉ የመንግስት አመራሮች ሊኖሩ ይችላሉ በማለት የሙስናውን በር ክፍት ከማድረጉ አንጻር፣ ትኩረት ለመሳብ ሲባል ብቻ አንድ ከፍተኛ የመንግስት አመራር ለእስር ሊዳረግ እንደሚችል ተጠርጥሯል፡፡