አውሮፓ ጥቅሟ ከተነካ በቀናት ውስጥ እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል – የአውሮፓ ሕብረት

አባይ ሚዲያ ዜና
በወንድወሰን ተክሉ

አዲሱ የአሜሪካ ጸረ-ሩሲያ ማእቀብ የአውሮፓን ጥቅም የሚጎዳ ሃሳብ ካለበት እኛም በቀናት ውስጥ የአጸፋ እርምጃ ለመውስድ ዝግጁ ነን ሲል የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን መግለጫ ሰጠ።

እንደ ጄን ክላውድ ጃንከር የህብረቱ ሰብሳቢ ከሆነ፣ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፊርማ የጸደቀው የጸረ-ሩሲያ ማእቀብ በጋዝ ማከፋፈሉ ስራ ላይ የተሰማሩትን የአውሮፓ ተቋሞችን ጥቅም የሚጎዳ ከሆነ አውሮፓም በተመሳሳይ መልኩ የጸረ-አሜሪካ እርምጃ እንደ አጸፋነቱ እንደሚወሰዱ ዝተዋል።

እረቡእ ነሀሴ 2 ቀን 2017 በፕሬዚዳንት ትራምፕ ፊርማ ወደ ተግባራዊ ሕግነት የተቀየረው ማእቀብ የሩሲያን ወታደራዊ ተቋም፣ ጋዝ፣ ማእድን እና የባቡር እንደሰትሪውን የሚጎዳ ሲሆን ማእቀቡ ከሩሲያ ጋር ንግድ የተለዋወጠን የሚቀጣ አንቀጽ ያካተተ በመሆኑ በሩሲያ ጋዝ አቅርቦት ላይ ጥገኛ የሆኑትን የአውሮፓ ሀገራት ክፉኛ እንዳስቆጣ ለማወቅ ተችሏል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሴኔቱና በኮንግረሱ አስገዳጅነት የፈረሙት የጸረ-ሩሲያ ማእቀብ “ከአለም አቀፍ ህግ ጋር የማይዛመድና ህገ-ወጥ”ሲሉ የገለጹት ሲሆን ሩሲያም በበኩሏ በ UN አምባሳደሯ ቫሲሊ ኒቤንዚ በኩል “ሩሲያ በአሜሪካን ማእቀብ ምክንያት አታጎበድድም -አትሰበርምም” [Russia will not “bend or break” over US sanctions] ካሉ በኋላ አክለውም “ፖሊሲዋንም ቢሆን አትለውጥም” [will not change its policy] በማለት መንግስታዊ አቋማን አሳውቃለች።

በዶናልድ ትራምፕ የተፈረመው አዲሱ ጸረ-ሩሲያ ማእቀብ ኢራን እና ሰሜን ኮሪያንም የሚያካትት ሲሆን እስከአሁን የአጸፋ መልስ እየተሰጠው ያለው ከሩሲያ በኩል ብቻ እንደሆነ እየታያ ያለ እውነታ ሲሆን ሩሲያ የማእቀቡ ኢላማ የሆነችበትም ምክንያት በዩክሬን ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባታና ክሪሚያን ወደ ግዛቷ በመጠቅለል፣ በሶሪያ ውስጥ ጣልቃ በመግባቷ እና ብሎም በ2016 የአሜሪካን ምርጫ ላይ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትን በመፈጸሟ ነው ተብሎ ቀደም ብሎ መገለጹ ይታወቃል።

ዲፕሎማቶችና ኤክስፕርቶች እርምጃውን በአውሮፓ ህብረት እና በአሜሪካን መካከል በታሪክ ተከስቶ በማያውቅ ደረጃ የንግድ ጦርነት ይከፍታል እያሉ ሲሆን ፕሬዚዳንት ትራምፕን ደግሞ በስልጣናቸው ያሻቸውን ማድረግ የማይችሉ መሆናቸውን በገሀድ ያወቁበት እርምጃም ነው ሲሉ ተደምጠዋል።