በአስቸኳይ ጥሪ የተሰየመው የህወሃት ፓርላማ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች አስቂኝ ናቸው የሚል አስተያየት እየተሰጠ ነው

0

ከሳምንታት በፊት ለክረምት ወራት እርፍት ወደየቤቱ ተሸኝቶ የነበረው የህወሃት መራሹ አገዛዝ ፓርላማ አባላት የእረፍት ጊዜያቸውን አቋርጠው በአስቸኳይ እንዲመለሱ ከተደረገ ቦኋላ  በዛሬው ቀን የተነጋገሩባቸው ጉዳዮችና ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች በሙሉ ምንም አይነት የአስቸኳይነት ባህሪ ያልነበራቸው ሆኖ መገኘታቸው ብዙዎችን ማነጋገር መጀመሩን ከቅርብ ምንጮች ለትንሳኤ ሬዲዮ ከደረሰው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

አገሪቱን የሚገዛው የህወሃት/ኢህአደግ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ እረፍት ላይ ለነበሩት  የፓርላማ አባላት ጥሪ ያደረገው በሳምንቱ መጀመሪያ አካባቢ ሲሆን ብዙዎች የተጠሩበት ጉዳይ በአሁኑ ሰዓት ነጋዴዎች ከጀመሩት ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ለአገሪቱ ችግሮች እልባት ለመስጠት የታሰበ ነገር ይኖራል ብለው እንዲገምቱ አድርጓቸው እንደነበር ይገለጻል። ዛሬ አርብ ነሃሴ 28 ቀን ማለዳ የፓርላማው ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት በትናንትናው ምሽት ላይ ለአባላቱ እንዲደርስ በተደረገው የስብሰባ አጀንዳ አንዳችም አጣዳፊ እና ዝግ ፓርላማ ለማስከፈት የሚያስቸኩል አንገብጋቢ ጉዳይ እንዳላገኙበት የሚገልጹት የፓርላማ ምንጮች ይህንን አግራሞታቸውን ለመግለጽ ሲባል አንዳንዶች በመደበኛ ስብሰባ ወቅት ተቃውሞ ወይም የድምጽ ታዕቅቦ ሊያደርጉበት በማይችሉባቸው የሹመትና ያለመከሰስ መብት በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የድጋፍ ድምጽ ሲነሱ መታየታቸውን ይነጋገራሉ። በዚህም የተነሳ በዛሬው ውሎ የተላለፉ ውሳኔዎች በሙሉ በአብላጫ ድምጽ ሆኗል።

በአስቸኳይ የተጠራው የኢህአደግ ፓርላማ በዛሬው ውሎው ተነጋግሮባቸው ውሳኔ አሳልፎአል ከተባሉት አጀንዳዎች አንዱ ከመስከረም ወር 2009 ጀምሮ ላለፉት አስራ አንድ ወራት ሥራ ላይ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሆነ ተገልጾአል። ይሁን እንጂ ፓርላማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በይፋ መነሳቱን ዛሬ ከማወጁ ቀደም ብሎ ነጋዴው ህብረተሰብ ወያኔ የቆለለበትን የዕለታዊ ገቢ ግብር ተመን አልቀበልም በማለት በጀመረው የሥራ ማቆም አድማና  እንደ አምቦ በመሳሰሉ ከተሞች ህብረተሰቡ መንገዶችን  በመዝጋትና የገዥው ፓርቲ ንብረቶች የሆኑ የትራንስፖርት አውቶብሶችንና ተሽከርካሪዎችን በማውደም ባሳየው ጀግንነት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  ያመጣል ተብሎ ይጠበቅ የነበረውን ውጤት ባዶ አስቀርቶታል። ከዚህም በተጨማሪ ህዝባችንን ለማፈንና ለመግደል ወያኔ ያሰማራቸው  የመከላኪያ ሠራዊት አባላትም በአብዛኛው ቦታዎች መሣሪያዎቻቸውን በገዛ ህዝባቸው ላይ ለማዞር ፍቃደኛ ሳይሆኑ ስለቀሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በወረቀት ላይ ካልሆነ በቀር ምድር ላይ ምንም አይነት ሃይል እንዳልነበረው የሚገልጹ ብዙ ናቸው ።

ህወሃት ምንተ እፍረቱን ዛሬ ለፓርላማው አቅርቦ መነሳቱን ያስወሰነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመጀመሪያው ስድስት ወር በኋላ ተደርጎ የነበረው የ4 ወር ተጨማሪ ጊዜ ገደብ ፓርላማው ከመሰየሙ አንድ ቀን በፊት ተቃጥሎ እንደነበር ይታወቃል።

በወያኔ አገዛዝ ስር የሚተዳደሩ ሚዲያዎች በዛሬው ዘገባቸው በአስቸኳይ የተጠራው ፓርላማ የአስቸኳይ ጊዜውን ከማንሳት ወሳኔ  በተጨማሪ የሶስት ሚንስትሮችን ሹመት እንዳጸደቀና በሙስና ወንጀል የተጠረጠረ የአንድ ግለሰብ ያለመከሰስ መብት እንደተነሳ ዘግበዋል። ይህም አጀንዳ ምንም አይነት አስቸኳይነት ባህሪ እንደሌለው  የፖለቲካ ተንታኞች አስተያየታቸውን እየሰጡበት ነው። በያንዳንዱ ሚንስትር መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በሹመት ከሚመደቡ ሚንስትሮች በተጨማሪ በሚንስትር ዴታ ወይም በምክትል ምንስትርነት የተመደቡ ሹሞች ስላሉ ፓርላማው የእረፍት ጊዜውን ጨርሶ እስኪመጣ ድረስ ሥራውን ሸፍነው መሥራት ሃላፊነት እንዳለባቸውና አስፈላጊ ውክልናም ካስፈለገ ጠቅላይ ሚንስትር ሆኖ የሚሠራ ሰው በደብዳቤ ውክልናውን መስጠት እንደሚችል የሚያረጋግጥ አሠራር አለ ተብሏል።

በዛሬው ዕለት ሹመታቸው የጸደቀው ሶስቱ ሚንስትሮች በቅርቡ በውለታና ከአካባቢው ዞር ለማድረግ ተብሎ በአምባሳደርነት ከተሾሙት መካከል በሚንስትርነት ሲሰሩ የነበሩትን ለመተካት እንደሆነ ታውቋል ።  በሃይለማሪያም ደሳለኝ አቅራቢነት የተሾሙት ሶስቱ ሚንስትሮች ከበደ ጫኔ የፌደራል አርብቶ ልማት ጉዳዮች ሚንስትር፤  ሞገስ ባልቻ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን ሚኒስትር እና ዶር ጥላዬ ጌቴ የትምህርት ሚኒስትር መሆናቸው ተገልጿል። ዶ/ር ጥላዬ ጌቱ  በትምህርት ሚንስትር ውስጥ ምንስትር ዴታ ሆኖ ሲያገለግል የኖረና በቅርቡ በአምባሳደርነት የተሾመውን አለቃውን እንዲተካ የተመደበ መሆኑንም ተያይዞ ከደረሰን ዘገባ ለማወቅ ተችሏል።

ሹመቱን አስመልክቶ አስተያየት እየሰጡ ያሉ ተንታኞች የመንግሥት ሹመት ለመስጠት ሲባል ፓርላማን ከእረፍት እስከመጥራት መድረስ በአገዛዙ ውስጥ ሥር እየሰደደ የመጣው ውጥረትና ሽኩቻ ምን ደረጃ እንደደረሰ አመልካች እንደሆነ ይገልጻሉ። በአምባገነንነታቸው የሚታወቁ አገዝዞች በሙሉ የህዝብ ተቃውሞ ሲበዛባቸው ሹም ሽር ማድረግ ባህሪያቸው ነው የሚሉ አካሎችም በተለይ እንዲህ አይነት አገዛዞች በመውደቂያቸው ሰሞን ሹም ሽር እንደሚያበዙ ወያኔም በእንደዚያ አይነት ችግር ውስጥ እየተዘፈቀ እንደሆነ ያስረዳሉ።

ህዝባዊ ተቃውሞ በአብዛኛው የአገራችን ክፍሎች እየተቀጣጠለ ከመጣ ወዲህ ወያኔ እየወሰደ ያለውን እርምጃ የሚከታተሉ አስተያየት ሰጪዎች ሁኔታው  በንጉሠ ነገሥቱ የመጨረሻ ዘመን ሆኖ ከነበረው ጋር ያመሳስሉታል። በጭፍን የስልጣን ፍቅር ሁሉንም ጠቅልለው የመግዛት ፍላጎት የነበራቸው ንጉሠ ነገስት በመጨረሻው የሥልጣን ዘመናቸው ከተማሪዎች ፤ ከሰራተኞችና ከሌሎችም የህብረተሰብ  ክፍል የተነሳባቸውን ተቃውሞ ለማርገብ የሚኒስትሮች ሹም ሽር አድርገው እንደነበር ሆኖም ግን ለውጥ ፈላጊው ህዝብ በጊዜው  “ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥ ” የሚል ተረት ተርቶባቸው ለመጨረሻው ግባተ መሬታቸው እንደዳረጋቸው ይታወሳል።