የህወሃት ሹም ሽርም ሆነ በሙስና ወንጀሎች ሎሌዎችን ወደ ዘብጢያ መላክ የህዝባችንን እውነተኛ የለውጥ ጥያቄ እንደማይመልስ የሚነገሩ ድምጾች እየበዙ ናቸው

0

በአስቸኳይ ስብሰባ ወደ መደበኛ ሥራው የተመለሰው የህወሃት ፓርላማ የመከሰስ መብቱን ያነሳው የኢህአደግ ሹም  የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚንስትር  ሚኒስትር ዲኤታ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ዓለማየሁ ጉጆ እንደሆነ ተገልጿአል።

አለማየሁ ጉጆ የመከሰስ መብቱ በተነሳ በሰዓታት ዕድሜ ውስጥ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉም በመገናኛ ብዙሃን ተዘግቧአል። ወያኔ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሙስና ወንጀል የተለያዩ ባለሥልጣናትን ወደ ወህኒ እየላከ እንደሚገኝ መዘገቡ ይታወሳል።

በሙስና ያልተጨማለቀ አንድም ከፍተኛ የመንግሥት ሹም በሌለበት አገራችን በአሁኑ ሰዓት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ እየተፈረደባቸው ያሉ ባለሥልጣናት ጠግበው አልታዘዝም በማለታቸው ይሁን ወይም መታዘዝ በዝቶባቸው እንቢ ማለት በመጀመራቸው የታወቀ ነገር የለም። የአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን የገነቡ የህወሃት የቀድሞ ተጋዳላዮችና የአሁኑ የጦር ጀነራሎች ወይም የሲቪል አስተዳዳሪዎች መካከል እስከ ዛሬ በሙስና የተጠረጠረቺው የአባይ ጸሃዬ ምስት ብቻ እንደሆነች ይነገራል።

ህወሃት የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት የሚፈጥሩ አባላቱን በሙስና ወንጀል ክስ እንደሚያሸማቅቅ እና ከርቸሌ እንደሚወረውር  ይታወቃል።