የህወሓት ሰራዊትን እየከዱ ወደ አጎራባች ሀገሮች የሚገቡት አባለት ቁጥር ያሰጋው አገዛዙ በተለይ ወደ ሱዳን የስደተኛ ካንፖች የሚያመሩት ኢትዮጵያውያን በሱዳን ፖሊሶች እየተደበደቡ ተላልፈዉ እንዲሰጡ ትዕዛዝ ማስተላለፉ ታወቀ

0

ከቅርብ ግዜ ወዲህ በተለይ በድንበር አካባቢ የሚሰፍሩ እና በአጎራባች አገራት በሰላም ማስከበር ስም ለግዳጅ የሚላኩ የህወሃት ሰራዊት አባላት በቡድን እና በነፍስ ወከፍ በመሆን ሰራዊቱን በመክዳት ላይ መሆናቸውን መረጃዎች አመለከቱ።

ወደ ግዳጅ ሄደው የሚጠፉ እና መሳሪያቸውን በየጫካው በመጣል በአጎራባች ሀገሮች ውስጥ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በመቀላቀል ተሸሽገዉ የሚኖሩ  የሰራዊት አባላት መኖራቸዉ መረጃ ደርሶናል በማለት የህወሃት ታማኝ ወታደሮች ከሱዳን ፖሊሶች ጋር በመተባበር ነዋሪው ማህበረሰብ ላይ ድብደባ እና እንግልት እያካሄዱ መሆኑን የአይን እማኞች ለትንሳኤ ሬድዮ ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል።

በተለይ በሱዳን የስደተኛ ካንፖች ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞች እንዳስታወቁት ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ ወደ ስደተኛ ካንፖች መጥተው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሱዳን ፖሊሶች ያላቸውን ገንዘብ እና ንብረት ተቀምተው እና ተደብደድበው ለህወሃት መንግስት ተላልፈው እንደተሰጡ ገልፀዋል። በካንፖቹ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ስደተኞች ፖሊሶቹን ጠይቀው እንዳገኙት መረጃ ከኢትዮጵያ መንግስት  ከዚህ በኋላ  ከኢትዮጵያ በድንበር በኩል  የሚገቡ ስደተኞች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እንዲያደርጉ  እና ሰዎችን  ከያዙ  በቀጥታ ለመንግስት እንዲያስረክቡ እንደተነገራቸው ገልጸውልናል ብለዋል። አክለውም የሱዳን ፖሊሶች አስቀድመው ከብዙ አመታት በፊት በካንፖቹ ዉስጥ ተጠግተዉ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንንም በካንፖቹ ሜዳ ላይ ቀልሰዉ ይኖሩበት የነበረውን የሳር ቤቶቻቸውን በላያቸው ላይ አፍርሰው ከካንፑ እንዳባረሩዋቸውም ተናግረዋል።

በሱዳን ውስጥ በሚገኙት 12 የስደተኛ ካንፖች ውስጥ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ኤርትራውያን ነን በማለት የሚኖሩ ሲሆኑ በአጋጣሚ ኢትዮጵያውያን መሆናቸዉ ከታወቀ ተደብድበዉ እንደሚባረሩ እና አብዛኛዎቹ እንደሚታሰሩም ስደተኞቹ ይናገራሉ። ከዚህ በፊት በተሳሳተ መረጃ ኢትዮጵያዊ ናችሁ ተብለዉ የተደበደቡ ኤርትራውያን ኤርትራዊ መሆናቸውን ከኤንባሲያቸዉ ማረጋገጫ በማምጣታቸው ከሱዳን መንግስት ካሳ እንደተከፈላቸውና “ይቅርታ፤ ኢትዮጵያውያን መስላችሁን ነው” የሚል  ደብዳቤ ተሰጥቷቸው እንደነበረም አስታውሰዋል።