ለጸጥታ ጥበቃ በሚል ምክንያት በአማራ ክልል ሰልጥነው የተሰማሩ የሚሊሺያ አባላት ቁጥር በመላው አገሪቱ ክልሎች ካሉት ጠቅላላ ድምር እንደሚበልጥ ታወቀ

0

የህወሃት መከላከያ ሚንስትር ሚኒስቴርና የኮማንድ ፖስት ዋና ሴክሬታሪ በመሆን በማገልገል ላይ ያለው ሲራጅ ፈርጌሳ በትናንትናው እለት ለአስቸኳይ ስብስባ ተጠርቶ ለነበረው ፓርላማ እንደገለጸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ በሆነባቸው አሥር ወራት ብቻ በአማራ ክልል 143459 (አንድ መቶ አርባ ሶስት ሺ አራት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ) የሚሊሺያ አባላት ሠልጥነው ተሰማርተዋል። ይህ የሚሊሽያ ቁጥር ለጸጥታ ጥበቃ በሚል ሽፋን በክልሉ እየተካሄደ የሚገኘውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመጨፍለቅ በክልሉ ተሰማርቶ የሚገኘውን የመከላኪያና ፖሊስ ሠራዊት ብዛት አንደማይጨምር ከመግለጫው ለመረዳት ተችሏል።

በአማራ ክልል አዲስ ሰልጥነው ከተሰማሩት ከነዚህ አንድ መቶ አርባ ሶስት ሺህ አራት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ የሚሊሺያ አባላት በተጨማሪ በአማራ፤ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች 16475 (አስራ ስድስት ሺህ አራት መቶ ሰባ አምስት) የፖሊስ አባላት አዲስ ሥልጠና እንደተሰጣቸው ሲራጅ ፌርጌሳ በሪፖርቱ ላይ ገልጿል።

በአሥር ወራት ዕድሜ ውስጥ ይህንን ያህል ብዛት ያለው የሚሊሺያ ሠራዊት በአማራ ክልል እንዲሠለጥን ሲደረግ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ስልጠና የተሰጣቸው ሚሊሺያ ቁጥር ይኑር አይኑር የተገለጸ ነገር የለም። ሆኖም ግን  ለኮማንድ ፖስቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች በአማራ ክልል ያለው የሚሊሺያ ብዛት በመላው አገሪቱ ካለው በእጅጉ እንደሚበልጥ በእርግጠኝነት ይናገራሉ።

ሲራጅ ፈርጌሣ በትናንትናው ዕለት ለምክር ቤት ተብየው የህወሃት ፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳም አስቸኳይ አዋጁ ያስፈለገበትን የአፈና እርማጃ የሚያስፈጽም ከፌደራል እስከ ክልል የተዘረጋው መዋቅር እንደሚቀጥልና በቅንጅት ለመሥራት ዕቅድ አውጥተው በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ አረጋግጧል።

ህወሃት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቶና ከአገሪቱ መከላኪያ ሠራዊት በተጨማሪ ይህንን ያህል ብዛት ያለው የሚሊሺያ አባላት አሠልጥኖ ባሠማራበት የአማራ ክልል የሚካሄደውን በመሣሪያ የታገዘ ህዝባዊ እምቢተኝነት ለመቆጣጠር ባለመቻሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መኖር እንዳልተጠቀመ አውቆ በሽምግልና ስም ከአማራ የተመለመሉ ካድሬዎችን በሽምግልና ስም ወደ ባህር ዳርና መቀሌ እያጓጓዘ ማወያየት እንደጀመረ  ይታወቃል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዋና ዓላማ ፍርሃትን በህብረተሰባችን ውስጥ በማስረጽ ምንም  አይነት ተቃውሞ እንዳይነሳ ማድረግ ሆኖ ሳለ በተለይ  በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተደጋግሞ በታየው የሥራ ማቆም አድማና መንገዶችን የመዝጋት እርምጃ አዋጁ እያስገኘ ካለው ውጤት ይልቅ ያስከተለው አለም አቀፍ ውግዘት በአገዛዙ ላይ ውጥረት እንደፈጠረ ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል።

ለህወሃት አገዛዝ ከፍተኛ የገንዘብና የፖለቲካ ድጋፍ የሚለግሱ የአውሮፓ ህብረት እና የአሜሪካን መንግሥት በተደጋጋሚ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ሲወተውቱ ከመቆየታቸውም በተጨማሪ በቅርቡ የአሜሪካ ምክር ቤት እንዲያጸድቀው ባለፈው ሳምንት በህግ መወሰኛው የአፍሪካ ጉዳይ ኮሚቴ ፊት ቀርቦ ውይይት የተካሄደበት H.Res 128 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአስቸኳይ እንዲነሳ የሚጠይቅ ረቂቅ ህግ እንዳለው ይታወቃል።

ሲራጅ ፌርጌሳ  ስለ አስቸኳይ ጊዜው አዋጅ መነሳት አስፈላጊነት ለምክር ቤቱ  መግለጫ በሰጠበት ወቅት አንዳንድ የኢህአደግ አባላት የአዋጁን መነሳት ተከትሎ ሊነሣ ስለሚችለው ህዝባዊ ተቃውሞ ስጋታቸውን ገልጸዋል። ሆኖም የኮማንድ ፖስቱ ያቋቋመው ከፈደራል እስለ ክልል ያሉ የጸጥታ አካላት መዋቅሮች በቅንጅት ስለሚሰሩ ምንም አይነት ስጋት የለም ሲል ስጋታቸውን ለማረጋጋት ሞክሯል።

በአፈናና ጭቆና ሥር የሚማቅቅን ህብረተሰብ በመሣሪያና ወታደራዊ ሃይል ገዝቶ እስከ ወዲያኛው ሥልጣን ላይ መቆየት የቻለ  አምባገነን ሥርዓት በየትኛውም አገር አልነበረም የሚሉ ኃይሎች ህወሃቶች ከደርግ ጋር ባደረጉት ትግል አገኘን የሚሉት ድል ለዚህ ማስረጃ እንደሆነ የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም።