በቃሊቲ እስር ቤት ዞን 6 በተባለው ቦታ የጅምላ ቀብር መገኘቱ እያነጋገረ ነው

0

ለትንሳኤ ዝግጅት ክፍል በደረሰው መረጃ መሠረት ሀምሌ 24/2009  የግቢው ሜዳ ተደርምሶ በርካታ አፅም ያለበት የጅምላ ቀብር መገኘቱን ለማወቅ ተችሏል። በዚህ ባልተጠበቀ ክስተት ምክንያት ለተደረመሰው ሜዳ  በቅርብ ርቀት የሚገኙ እስረኞች ወደ ሌላ ክፍል እንዲዛወሩ ተደርገዋል ተብሏል።

በሁኔታው የተደናገጡ የእስር ቤቱ ሃላፊዎች የጅምላ መቃብሩ የተገኘበትን ስፍራ ወዲያውኑ በቆርቆሮ በመከለል ሰው እንዳያየው ለማድረግ ከመሞከራቸውም በላይ የተደረመሰውን ቦታ ለመድፈን  አሸዋና ጠጠር በማስመጣት ሜዳው ላይ እንዲራገፍ ማድረጋቸው ተገልጿል። አሸዋው የተራገፈበትን ቦታ እስረኞችን ለመጠየቅ ወደ ዞን 3 የሚሄዱ ጎብኝዎች ሁሉ ሊያዩት እንደሚችሉም መረጃው ያመለክታል።

የጅምላ ቀብሩን ያዩ የእስር ቤቱ ታሳሪዎች ምናልባት ድህረ ምርጫ 97 በእስር ቤቱ ከታሠሩ ቦኋላ በ1998 እስር ቤቱ ውስጥ በተፈጸመው ጭፍጨፋ  የተገደሉ እስረኞች ሊሆኑ እንደሚችል ግምታቸውን እየገለጹ ነው። አንዳንዶች ደግሞ የኦጋዴንና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባል ናችሁ እየተባሉ ታስረው ወደ ቃሊቲ ከመጡ በኋላ የደረሱበት ያልታወቁ ሰዎች አስከሬን ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ገልጸዋል።

ህወሃት ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ወደ ተለያዩ እስር ቤት በሚያግዛቸው እስረኞች ላይ በሚፈጽመው ድብድባና ሰቆቃ  እስር ላይ እያሉ ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ሲገለጽ መኖሩ ይታወሳል። በቅርቡ ታስረው በሚገኙበት ክፍል ውስጥ ሆን ብሎ በተቀሰቀሰ የእሳት አደጋ በርካታ ሰዎች መገደላቸው በተለያዩ ሚዲያዎች ሲገለጽ እንደነበር ይታወቃል።