የንግድ ተሽርካሪዎች ላይ የተጣለዉ የግብር ጭማሪ በትራንሰፖርት ግልጋሎት ላይ እክል እየፈጠረ መሆኑ ተገለፀ

0

በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች ከደረጃ  “ሐ” ግብር ከፋዮች ጋር ተመድበዉ የተጣለባቸዉን ከፍተኛ የግብር መጠን እንዲከፍሉ ጫና እየተደረገባቸዉ  ያሉ የንግድ ተሽከርካሪዎች ከግብር ጭማሪዉ ጋር በተያያዘ በነዳጅ እጦት እና በመለዋወጫ እቃዎች ዋጋ መናር ችግር ውስጥ መግባታቸውን በመናገር ላይ ይገኛሉ። በደረጃ “ሐ’  የንግድ ተሽከርካሪ ምድብ የተመደቡት ኮድ አንድ እና ለከተማ ግልጋሎት የሚዉሉ የሚኒባስ እና የዉይይት ታክሲዎች እንዲሁም የባጃጅ ተሽከርካሪዎች ሲሆኑ የቀን ገቢ ተመን አሰጣጡን በተመለከተ እንደሸቀጣሸቀጥ ባለሱቆች ሁሉ ለተወሰኑ ክልሎች እና አካባቢዎች ተመኑ የተሰጠዉ በተለያየ ጊዜ ሲሆን ጭማሪዉም ከቀድሞዉ በሁለት እጥፍ የሚበልጥ መሆኑም ታዉቋል። በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በደሴ እና በድሬዳዋ የንግድ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ግብሩን የሀምሌ ወር ከመጠናቀቁ በፊት እንዲከፍሉ ከፍተኛ ግፊት እና ማስፈራሪያ  እየተደረገባቸዉ መሆኑን ገልፀዉ ያልተመጣጠነዉን  የግብር ጭማሪ አመቱን ሙሉ የነበረዉን የነዳጅ እጥረት አና የመለዋወጫ እቃ  ችግር በመጥቀስ አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል።

የተከሰተዉን የነዳጅ እጥረትን ተከትሎ በተለይ በአማራ ክልል ሹፌሮች አብዛኛዉን ግዜ ነዳጅ የሚገዙት ከነዳጅ ማደያዎች ሳይሆን የማደያ ባለቤቶች በጀርባ ከሚያስረክቧቸዉ የችርቻሮ ሱቆች መሆኑን አስታዉሰዉ በተለይ በጎንደር እና በባህር ዳር አካባቢ  የተለመደ ድርጊት መሆኑን በማስረዳት በአንድ ነዳጅ ማደያ ነዳጅ መራገፉ ከታወቀ ለአንድ ቀን ወይም ግፋ ቢል ለሁለት ቀናት ብቻ ተጠቃሚዉ ከገበየ በኋላ  ማደያዎች ለችርቻሮ ባለሱቆች በጄሪካን 10 ብር ጭማሪ በማድረግ በጓሮ በኩል እንደሚያስረክቡ እና ወዲያዉኑ ነዳጅ አልቋል አንደሚባል ገልፀዋል፡፡

ነዳጅ ከማደያ በሁለት ቀናት ዉስጥ ሲያልቅ በችርቻሮ ሱቆች ዉስጥ ግን ከወር እስከወር በጨመረ ዋጋ እንደሚሸጥ እና ከዚ በፊት ተጠቃሚዉ ባደረገዉ ጥቆማም የተወሰኑ ነዳጅ ቸርቻሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ቢሆንም ወዲያዉኑ ገንዘብ በመክፈል ተለቀዋል ብለዋል። አያይዘዉም ከተጣለዉ የቀን ግብር ጋር በተያዘ የመለዋወጫ እቃ መሸጫ ሱቆች ዋጋ ጭማሪ በማድረግ ላይ በመሆናቸዉ የገጠማቸዉን ፈተና አክበዶታል በማለት ይገልፃሉ።

በዚህም ምክንያት መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም በተለይ በክልል ከተሞች የሚኖሩ የተሽከርካሪ ባለቤቶች የተጣለዉ የግብር ጭማሪ አግባብ ነዉ ብለዉ ስለማያምኑ አብዛኛዎቹ ላለመክፈል በመወሰን ያገዛዙን ዉሳኔ በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜናም በመንግስት መስሪያ ቤቶች ለአባይ መዋጮ በሚል በየወሩ ይከፍሉ የነበረዉ መጠን ላይ  ያለ ሰራተኛዉ ፈቃድ ጭማሪ ለማድረግ እቅድ  ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየሆነ እንዳለ መረጃዎች እያመለከቱ ነዉ። አገዛዙ በዚህ አመት ከነጋዴዉ ላይ በጭማሪ ግብር ሰበብ  ለመሰብሰብ አቅዶ የነበረዉን ገንዘብ ለማግኘት እንደማይሳካለት ሁኔታዎች እያመላከቱ ስለሆነ፤ ከመንግስት ሰራተኛዉ ላይ በተለያዩ መዋጮዎች ሰበብ ከደሞዙ ላይ ተቆራጭ ማድረግ  እንደ ሁለተኛ እቅድ መያዙን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸዉ ምንጮች ገልፀዋል።