መቼም አንረሳችሁም!!!

0

ከሰማያዊ ብሔራዊ ሸንጎ የነሐሴ 01 ቀን 2008 ዓ.ም ሰማዕታትን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

የአለፈው 2008 ዓ.ም ለኢትዮጵያውያን የመራራ ሀዘንና የጨለማ ዘመን ነበር፡፡ በባህር ዳር ከተማ ነሐሴ 01 ቀን 2008 ዓ.ም በኢትዮጵያ የማንነት፣የነፃነት፣የፍትህና የእኩልነት ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ ባዶ እጃቸውን ለተቃውሞ የወጡ ዜጎች ላይ የገዥው ቡድን አልሞ ተኳሾች በከፈቱት የተኩስ እሩምታ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተሰውተዋል፡፡ በዚህ አረመኒያዊ ድርጊት የብዙዎች ቤት ተዘግተዋል፣አሮጊቶች ያለጧሪ ቀባሪ ቀርተዋል፣ህጻናት ያለአሳዳጊ ተበትነዋል፣ እናቶች የልጆቻቸውን አባት ተነጥቀዋል፣ አባቶች የልጆቻቸውን እናት ተነጥቀዋል፣ለሀገሬና ለወገኔ ብለው ለእውነት የጮሁ ለጋና ታዳጊ ወጣቶች በገዥው ጥይት ተቀጭተዋል፡፡ በአጠቃላይ በዛች ዕለት በባህር ዳር የተፈፀመው የጅምላ ግድያ ታሪክ ይቅር የማይለው መሪር ሃዘኑም ከብዙ ኢትዮጵያውያን ልብ ሊጠፋ የማይችል ዘግናኝ የጭካኔ ተግባር በአገዛዙ ተፈፅሟል፡፡

ይህንን የባህር ዳር ጭፍጨፋ ቀኑን ምክንያት በማድረግ በተለየ ሁኔታ ዘከርነው እንጂ ከነፃነት እና እኩልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በአማራ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያየ ጊዜ በርካታ ኢትዮጵያውያን የደም መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ በኮንሶ ብዙ ኢትዮጵያውያን ቤታቸው እየተቃጠለና በአገዛዙ ጥይት እየተደበደቡ ተገድለዋል፡፡

አገዛዙ በዘራው የጥላቻ ፖለቲካ ምክንያት በጌዲኦ ብዙ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የነፃነትና የእኩልነት ጥያቄ ያነሱ ኢትዮጵያውያን በአገዛዙ ጥይት እየተደበደቡ ተገድለዋል፡፡ እናት በልጇ አስከሬን ላይ እንድትቀመጥ ተደርጓል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ አገዛዙ በፈጠረው ችግር በኦሮሞዎች ዓመታዊ የኤሬቻ በዓል ላይ ሳይቀር ኢትዮጵያውያን በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ለራሱ ዜጎች የማይራራውና በአልሞ ተኳሽ ለተቃውሞ የወጡ ዜጎችን በጭካኔ የሚገድል አገዛዝ ለሀገር ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ደንታ የሌለው አገዛዝ ከደቡብ ሱዳን ለመጡ የሙርሌ ጎሳዎች በሩን ወለል አድርጎ ከፍቶ ከአንድም ሁለት ጊዜ በጋምቤላ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን በጥይት ተደብድበው ህይወታቸውን አጥተዋል፣ህፃናት ከወላጆቻቸው ተነጥቀው በሙርሌዎች ተወስደዋል፡፡
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ነፃነትና እኩልነት እውን እንዲሆን እና ህዝባዊ አስተዳደር እንዲመሰረት ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች የመጨረሻ ውድ የሆነውን የህይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ እኛም እናንተ የጀመራችሁት የነፃነትና የእኩልነት ጥያቄ ከዳር እስኪደርስ ድረስ በደማችሁ የሰጣችሁንን ቃል ኪዳን መቼውንም አንረሳውም፡፡ እናንተ በተግባር በመሰዋዕትነት ያሳያችሁንን አርዓያነት በኩራት ለመፈፀም ሁልጊዜም ዝግጁ ነን፡፡ አኩርታችሁናልና ቃላችንን አናጥፍም፡፡ ውድ ህይወታችሁን የከፈላችሁላት ሀገራችሁም በአኩሪ ታሪክ ለዘላለም ትዘክራችኋለች፡፡

በመጨረሻም በእነዚህ ጀግኖች መስዋዕትነት የተቀጣጠለውን የነፃነት ችቦ በመረከብ የተነሱለትን ዓላማ ከዳር ለማድረስ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ያለበትን ታሪካዊ የዜግነት ሃላፊነትና ግዴታ እንዲወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
ሐምሌ 30 ቀን 2009 ዓ.ም
አዲስ አበባ