በሰማእታት ቀን ዋዜማ በባህር ዳር ሁለት ቦንብ መፈንዳቱ ተገለጸ

አባይ ሚዲያ ዜና
በወንድወሰን ተክሉ

በዛሬው እለት በባህርዳር ታስቦ የሚውለው የሰማእታት ዝክር እለት ከመፈጸሙ በፊት በዋዜማው ምሽት በባህር ዳር ሁለት የእጅ ቦንቦች በብአዴን ጽ/ቤት አቅራቢያ መፈንዳቱ ከስፍራው በደረሰን መረጃ መሰረት ማወቅ ተችሏል።

በቦንብ ጥቃቱ የደረሰውን ጉዳት ለግዜው ማወቅ ያልተቻለ ሲሆን ሃላፊነቱንም የወሰደ እስካሁን የለም። ሆኖም የፌዴራል ሰራዊት ከተማይቱን በመውረር በአደጋው ፍራቻ የቤት ለቤት አሰሳ ማጧጧፋቸውን ኢሳት ዘግቧል።

ቀደም ሲል እንደገለጽነው በባህር ዳር ነሀሴ 1 ቀን 2008 ዓ.ም በአግዓዚ ሰራዊት የተጨፈጨፉትን ከ50 በላይ ንጹሃንን ለመዘከር ህዝቡ ጥሪ በማስተላለፉ የህወሃት ባለስልጣናት የትግራይ ተወላጆችን ለደህንነታችሁ አስጊ ነው በማለት ወደ መቀሌ እንዳጓጓዛቸው መግለጻችን ይታወሳል።

ዛሬ ማምሻውን በባህር ዳር ቀበሌ 11 በብአዴን ጽ/ቤት አቅራቢያ ሁለት የእጅ ቦንቦች በተከታታይ እንደፈነዱ ማወቅ የተቻለው ከተማዋን የወረሩት የፌዴራል ፖሊስ በየቤቱ ጥብቅ ፍታሻን እያጧጧፉ ባለበት ወቅት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ቀደም ባሉት ቀናት የባህርዳር ወጣቶች የወገኖቻችንን ጭፍጨፋ ለመዘከር በጠራነው የስራ አድማ ላይ እንቅፋት ሊሆን የሚፈልግ ለሚደርስበት ቅጣት ተጠያቂው እራሱ ነው ብለው በራሪ ወረቀት ማሰራጨታቸው የሚዘነጋ አይደለም።