አባይ ሚዲያ ዜና
አክሊሉ ታደሰ

ከአሜሪካ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ሁለት አመት በኋላ በሚደረገው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤቶች አባላት ምርጫን አስመልክቶ አቶ አሌክሳንደር አሰፋ የዲሞክራት ፓርቲን ወክለው ለኔቫዳ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እጩ ተወዳዳሪ ሆነው መቅረባቸው ታወቀ፡፡

አቶ አሌክሳንደር ባለፈው ሀሙስ ማታ በላስቬጋስ ነዋሪ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን በተዘጋጀ የራት ግብዣ ላይ ተገኝተው ለኔቫዳ ስቴት ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እጩ ተወዳዳሪ መሆናቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት በተለይ እኛ ኢትዮጰያወያን እንደብዛታችን በአሜሪካ ዜግነታችን ልናገኛቸው የሚገቡንንና የኑሮዋችንን ጥራት ሊቀይሩ የሚችሉ መብቶቻችንን ለማስከበር ከመስራት ይልቅ የተሰጠንን ብቻ በመቀበል በመኖራችን እያለን እንደሌለን አስቆጥሮናል በማለት ጠቅሰው ይህንንም ሁኔታ ለመቀየር ዋነኛው መንገድ በምርጫዎች ላይ ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዲሞክራትን ወክለው በእጩነት የቀረቡት አቶ አሌክሳንደር በምርጫዎች ባለመሳተፋችንና እንደ ብዛታችን ድምጻችንን ተጠቅመን መብቶቻችንን የሚያስጠብቁና የሚያስከብሩ ተወካዮች እንዲመረጡ ባለማድረጋችን ያጣናቸውን ነገሮች በምሳሌነት በማንሳት በአሜሪካ ምርጫዎች ተሳታፊ የመሆንን አስፈላጊነት ለታዳሚው ሲያስረዱ ይህ ሁኔታ እጩ ተወዳዳሪ ለመሆን ካነሳሱዋቸው ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ አሌክስ በምርጫ ባለመሳተፋችን ያጣናቸውንና በምርጫ የመሳተፍ አስፈላጊነትን አስመልክቶ ከሰጡት ማብራርያ በተጨማሪ ከፊታቸው በሚጠብቃቸው የምርጫ ቅስቀሳ እስከ ድምጽ መስጠት ድረስ ማህበረሰባችን ከጎናችው እንዲቆም ጥሪ ማድረጉን ተከትሎ ከታዳሚውም በኩል ሞቅ ያለ ድጋፍ ተችሯቸዋል፡፡

በመጨረሻም እስከአሁን ከጎናቸው በመሆን ድጋፋቸውን ለሰጧቸውና ጥሪያቸውን አክብረው በቦታው በመገኘት ድጋፋቸውን የሰጧቸውን ታዳሚዎች አመስግነዋል፡፡

ማሳሰቢያ፤-  ወደፊት ከአቶ አሌክሳንደር አሰፋ በአባይ ሚዲያ የቀጥታ ስርጭት የምናደርገውን ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ ይዘን እንደምንቀርብ ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡