ባሕር ዳር አንደኛ ዓመት የሰማእት ቀን በስራ አድማ እየዘከረች ነው

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በነሀሴ 1ቀን 2008ዓ.ም በባሕር ዳር በአግዓዚ ሰራዊት በግፍ ለተጨፈጨፉት ሰማእታት መታሰቢያ ዛሬ ነዋሪው በስራ ማቆም አድማ በማሰብ ከቤት በመዋል እየዘከረ ሲሆን የፌዴራል፣የክልሉ ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት ለማስገደድ ያደረጉት ሙካራ እንዳልተሳካ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በጎንደር ደብረ ታቦርና በወሎ ወልዲያ በባህር ዳር ያለቁት ወገኖቻችን ናቸው፣ለነፍሰ ገዳዩ መንግስትም ግብር አንገብርም በማለት እለቱን በስራ አድማ ማቆም ተግባር ከባህር ዳር ጋር እንደተቀላቀሉ ለማወቅ ተችላል።

በባህር ዳር በፌዴራልና በመከላከያ ሰራዊት አዛዦች በርእሰ መስተዳድሩ ጽ/ቤት በተደረገ ስብሰባ የባጃጅ እና የከተማዋን ታክሲ አሽከርካሪዎች አስገድዶ ወደ ስራ ለማሰማራት ታስቦ የነበረ ሃሳብም ከስምምነት ባለመደረሱ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርታል።

በከተማዋ መግቢያና መውጪያ የፌዴራሉና የመከላከያው ወታደሮች የታጠቀ ሃይል ወደ ከተማዋ ይገባል በሚል ስጋት በተጠንቀቅ እየተጠባበቁ እንዳለ ከባህርዳር የደረሰን መረጃ የሚያመለክት ሲሆን ከትናንት ማታ ጀምሮ በከተማዋ የፈሰሰው የሰራዊት መንጋም የነዋሪውን ህዝብ የሰማእታቱን ዝክር የተቃውሞ አድማ ከማድረግ እንዳላገደው መረዳት ተችላል።

image

ባህር ዳር ዛሬ ሙሉ በሙሉ ጭር ብላ እንደለች ለማወቅ የተቻለ ሲሆን የንግድ ቤቶች፣የከተማዋ ታክሲዎችና ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች እገልግሎታቸውን ባለመስጠት የአድማው ተሳታፊ ሆነው ተገኝተዋል።

በባህር ዳርና በአንዳንድ የአማራ ከተሞች እየተካሄደ ያለው የዛሬው የስራ ማቆም አድማ ነሀሴ 1ቀን 2008 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ በወጣው ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የአግዓዚ ሰራዊት በወሰዱት የግፍ እርምጃ ከ50በላይ ንጹሃን፣አብዛኞቹ ወጣቶች የተጨፈጨፉበትን ለመዘከር እንደሆነ ይታወቃል።