የኬኒያ ሙስሊሞች በጨረቃ ላይ በታየ እንግዳ ክስተት የምርጫው አስፈሪነት ነው አሉ፣ ኬኒያውያን ፈርተዋል

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በናይሮቢ፣ በጋሪሳ እና በማንዴራ የሚኖሩ ሙስሊም ኬኒያውያን ዛሬ ምሽት ላይ በጨረቃ ላይ ባዩት ያልተለመደ እንግዳ ክስተት ነገ የሚካሄደው ምርጫ አደጋ እንዳለው ምልክት ነው ሲሉ ማምሻውን ለጸሎት ወደየመስጊዱ ሲጣደፉ ለማየት ተችሏል።

በኬኒያ ግዛት ላይ የታየችው ጨረቃ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በጥቁር ጨለማ የተከበበችና የተሸፈነች በመሆን ከምሽቱ 2:45 እስከ 3:30 ድረሰ የታየች ሲሆን ነዋሪው ምልክቱን ነገ ከሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ጋር በማያያዝ የአደጋ ምልክት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ናይሮቢ እጅግ በሚደንቅ ሁኔታ ዛሬን በጭርታ ተሞልታ የዋለች ሲሆን አብዛኞቹም የንግድ ተቋሞች ድርጅታቸውን ለአገልግሎት ሳይከፍቱ መዋላቸው የታየ ሲሆን ብዙዎች ደግሞ በምርጫው ማግስት ይነሳል ብለው ለተነበዩት ግጭትና የእርሰበርስ ጦርነት እራሳቸውን ለማዳን ወደየቤተሰቦቻቸው ሲሄዱ ተገኝተዋል።

ነገ የሚካሄደውን የኬኒያን ሀገር አቀፍ ምርጫን ለመታዘብ አሜሪካ በጆን ኬሪ የሚመራ የታዛቢ ልኡካን ቡድን ስትልክ የአፍሪካ ህብረትም በበኩሉ በቀድሞው የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ታቦ እምቤኪ የሚመራ ታዛቢ ልኡካን እንደላከ ታውቋል። የአውሮፓ ህብረትም በተመሳሳይ መልኩ ከመቶ በላይ ታዛቢ መላኩ ታውቋል።

በመንግስትና በተቃዋሚው በኩል ምርጫው ሰላማዊ ነጻ እና ተዓማኒነት ባለው ግልጽነት ይፈጸማል ብለው ለኬኒያውያኑ ተስፋ ቢሰጡም ሕዝቡ ግን የኬኒያን የምርጫ ታሪክ በማጣቀስ ይህ የዘንድሮ ምርጫ በሰላም የሚጠናቀቅ አይደለም ሲሉ በአቋማቸው ጸንተዋል።

እንደ ኬኒያውያኑ አባባል ኬኒያ ለመጀመሪያ ግዜ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት አውጅ በ1992 ያካሄደችውን ምርጫ በሰላም መጠናቀቁን ጠቅሰው ቀጥሎ በተካሄደው የ1997 እና ከዓስር ዓመት በኋላ በ2007 በተካሄደው ምርጫ በተፈጠረ የእርሰበርስ ጦርነት ከፍተኛ ውድመት መከሰቱን ይገልጻሉ።

አያይዘውም በ2002 እና በ2013 በተካሄዳው ምርጫ አንጻራዊ ሰላም መሆኑን አውስተው ዘንድሮ ግን፤ ይላሉ ኬኒያውያን፣ ከ2007ቱ ደም አፋሳሽ ዓስረኛ ዓመት ላይ በመሆኑና ብሎም የባለፈው የ2013ቱ በሰላም የተጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰው የ2017ቱ ደም አፋሳሽ ይሆናል ባይ ናቸው።

የኬኒያውን ፍርሃትና ስጋት የሚያጠናክሩ ግብዓቶች በዘንድሮው ምርጫ ላይ የተንጸባረቀ ሲሆን ይህም በህይወታቸው ለ4ኛ ግዜና ብሎም ለመጨረሻ ግዜ ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት ተቃዋሚው መሪ አቶ ራይላ ኦዲንጋ የማይናወጽ ጽኑ አቋም ሲሆን ሰውዬው የሚቀጥለው ፕሬዚዳንት መሆን የምችለው እኔ ነኝ በሚል እምነት መገኘታቸውና በአንጻሩም በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ከተሸነፉ ስልጣናቸውን ለመስጠት ዝግጁ አይደሉም ተብሎ በሰፊው መነገሩ የነገውን ምርጫ ለኬኒያውያኑ እና በኬኒያ ለሚኖሩትም አስጊና አስፈሪ እንዳደረገው መረዳት ተችሏል።

ማምሻውን በጨረቃይቱ ላይ የታየውን እንግዳ ጥቁር ክስተትንም ሙስሊም ኬኒያውያኑ ከምርጫው ጋር በማያያዝ ለጸሎት ወደ የመስጊዱ ሲሮጡ ለማየት ተችሏል።