ሕሊናን የሚሞግት መልእክት(ያዕቆብ ኃ/ማርያም (ዶ/ር) )

0

ይህ ‹ከህወሓት ሰማይ ሥር› የተሰኘው መጽሐፍ ብዙ ርዕሰ ጉዳዮችን የያዘና በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ጥልቅ ዕውቀት የሚያጎናፅፍ ነው፡፡ ፍርሀትና አደርባይነት በማያውቅ ብዕር የተከተበ በመሆኑ አገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን በሚተነትንበት ጊዜ ግልጥና የማያሻሙ እውነታዎችን አደባባይ ያወጣል፤ አንድም ከዚህ በፊት ይፋ ያልሆኑ የህወሓት ኢህአዴግ ሥውር የፖለቲካና የኢኮኖሚ አጀንዳዎችን የሚያጋልጥ በመሆኑ ለአንባቢ ሰፋ ያለ ግንዛቤ ያስጨብጣል፡፡

book-cover

ጸሐፊው ቀደም ሲል በህወሓት ኢህአዴግ ጓዳ በተሰየመበት ጊዜ የታዘባቸውን ፖለቲካዊ ሸፍጦች፤ ኢ-ዲሞክራሲያዊ የአፈናና የጠቅላይነት እንቅስቃሴዎችን እንደወረደ ማቅረቡ ሕዝቡ የህወሓት ኢህአዴግን ማንነት እንዲረዳ በማናቸውም መንገድ ሊተካ የማይችል ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡

የስነ-ቋንቋው ጥራትና የቃላት አጠቃቀሙ ከጥልቅ የሁኔታዎች ትንተና ብቃቱ ጋር ተዳምሮ ማንም ሰው መጽሐፉን ማንበብ ከጀመረ ንባቡን ለአፍታ እንኳን እንዳያቋርጥ የማስገደድ የተለየ አቅም አለው፡፡ ይህ የጸሐፊው ውጤት ለኅትመት በቅቶ ለሕዝቡ ቢደርስ ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን ከመስጠቱ ባሻገር ተተኪ ባለስልጣናት ወይም ተተኪው መንግሥት የህወሓት ኢህአዴግን ፀረ-ዴሞክራሲያዊ፡ የጨለማና የቁልቁለት ጉዞ እንዳይደግም በቂ ግንዛቤ ሊፈጥርለት ይችላል፡፡

ሀብታሙ አያሌው ከወህኒ ቤት ስቃይና ያንን ተከትሎ ነፍሱን ለመንጠቅ ተቃርቦ ከነበረው ህመሙ ሳያገግም እንዲህ ያለ መጽሐፍ ጽፎ ለሕዝብ ለማቅረብ ያሳየው ብርታት ለሁላችን ሕሊናን የሚሞግት መልእክት ሁሉ እንዳለው ይሰማኛል፡፡

            ያዕቆብ ኃ/ማርያም (ዶ/ር)