በየመን 50 የሚደርሱ ስደተኞች በተንኮል ወደ ባህር እንዲሰምጡ ተደረጉ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ጋሻው ገብሬ

አልጃዚራ ዛሬ እንደዘገበው በየመን 50 የሚደርሱ ስደተኞች በተንኮል ወደ ባህር እንዲሰምጡ ተደረጉ።

ሰው አሻጋሪው ደላላ ሆን ብሎ ሶማሌዎችንና እትዮጵያውያንን ለይቶ የመን መዳረሻ ሲቃረቡ እያስገደደ ባህር እንዲገቡ አድርጓቸዋል። የተባበሩት መንግስታት የስደተኛ መስሪያ ቤት ድርጊቱን “ዘግናኝና ኢሰብአዊ” ብሎታል።

ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (International Organization for Migration (IOM) በችኮላ የተማሰ መቃብር ውስጥ በሻብዋ የመን የውሃ ዳርቻ 29 ስደተኞች ተቀብረው አግኝቷል። 22 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አይታወቅም። የስደተኞቹ አማካይ እድሜ 16 ዓመት ነው ይላል ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት።

የመን በርስበርስ ውጊያ የታመሰች ብትሆንም ለአፍሪካ ባላት ቅርበት የተነሳ የስደተኞች መተላለፊያ መንገድ ሆናለች። ስደተኞቹ ተስፋ የሚያደርጉት በዘይት ሃብት የበለጸጉት አረብ አገሮች መድረስን ነው። ደላላው 120 ሰዎችን የመን ሲዳረሱ አስገድዶ አስወርዷቸዋል ይላል ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት የሰጠው መግለጫ።

ሎረንት ቦእክ የተሰኘ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ሰራተኛ ደላላው “አለቃ መሰል” ሰዎችን ከሩቅ ሲያይ ስደተኞቹን ገፍትሮ ከባህር ጣላቸው በማለት የተረፉት ሰዎች እንደነገሩት ገልጿል።

ያው ደላላ ይህኑ ተግባሩን ለመቀጠልና ሌሎች ስደተኞችን ለማሻገር ወደ ሶማሊያ ተመለሰ ብለዋል ከመከራው የተረፉት ስደተኞች።