በማሊ የተከሰከሰው የጀርመን ተዋጊ ሄሊኮፕተር በጠላት ለመመታቱ ማረጋገጫ አልተገኘም ተባለ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

የጀርመን መከላከያ ሚኒስቴር ስሪቱ የኤየር በስ (Airbus) የሆነ ተዋጊ ሂሊኮፕተር በሰሜናዊ ማሊ በግዳጅ በሚበርበት ወቅት ተከስክሶ መውደቁን ማስታወቁ ይታወሳል።

የጦር ሂሊኮፕተሩ የተከሰከሰበትን ትክክለኛውን መንስኤ ለማወቅ ተጨማሪ ወራቶች እንደሚጠይቅ የሚኒስቴር ቤሮው ባሳለፍነው እሮብ በሰጠው መግለጫ አሳውቋል።

ባሳለፍነው ወር ማገባደጃ በማሊ የሰላም የማስከበር ግዳጅ ለተሰማሩት ወታደሮች ድጋፍ ለመስጠት ሲበር የነበረው ይህ ተዋጊ ሂሊኮፕተር በአየር ላይ ሳለ መሰባበር መጀመሩ ምን አልባት የቴክኒክ ችግር ሳያጋጥመው እንደማይቀር እየተገመተ ይገኛል።

የጀርመን የመከላከያ ሚንስቴር ባለስልጣናት በበኩላቸው ሂሊኮፕተሩ በጠላት ተመትቶ ስለመከስከሱ የሚያሳይ ምንም አይነት ማረጋገጫ እንዳላገኙ እየተናገሩ ይገኛሉ።

የዚህ የሂሊኮፕተር መከስከስ ከፓይለቶች የብቃት ደረጃ ጋር እንደማይገናኝም የጀርመን መከላከያ ሚኒስቴር ለሚዲያ በሰጡት ቃል አረጋግጠዋል።

የሂሊኮፕተሩ አምራች የሆነው ኤየር በስ (Airbus) የአደጋውን መንስኤ ተከትሎ ለተጠየቀው ጥያቄ መልስ ከመስጠት በመቆጠብ በሚደረገው ምርመራ ግን ትብብር እንደሚያደርግ አሳውቋል።

አደጋውን ተከትሎ የጀርመን መከላከያ ሚኒስቴር ከኤየር በስ የተመረቱትን ተመሳሳይ ተዋጊ ሂሊኮፕተሮች ላልተወሰነ ጌዜ ከመጠቀም እንደተቆጠበ ገልጿል።

በአደጋው ህይወታቸው ያለፉት ሁለቱ ጀርመናዊ ወታደሮች በወታደራዊ ስነስርአት በክብር መቀበራቸውም ታውቋል።

በማሊ በመንግስትና በተቃዋሚ ሚሊሺያ ግሩፕ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ወታደሮችን እንዳሰፈረ ይታወቃል።