ኢ-ፍትሃዊው የግብር ተመን በክልሎቸ መካከል በተለያየ መንገድ እንደተተመነ ታወቀ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በአነስተኛ የንግድ ካፒታል በሚነቀሳቀሱ ነጋዴዎች ላይ የተተመነው ኢ-ፍትሃዊው የግብር ተመን በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች እኩል የተተመነ ሳይሆን በተወሰኑ ክልሎች ብቻ ሆን ተብሎ የተተመነ መሆኑ ከተለያዩ ክልሎች ያሰባሰብነው መረጃ መረዳት ተችሏል።

በኬኒያና ኢትዮጵያ የድንበር ከተማ በሆነችው ባለሁለት ቀበሌዋ ሞያሌ ክልል 4 [ኦሮሚያ ክልል] ስር ባለው ቀበሌ የሚኖሩ ነጋዴዎች እንደገለጹልን ከሆነ ከተማዋ በተተመነው ኢ-ፍትሃዊ የግብር ተመን ጫና በሚጮሁ ነጋዴዎች እና በሚጮሁት ላይ በሚሳለቁ ነጋዴዎች ለሁለት ተከፍላለች ብለዋል።

የኢትዮ-ኬኒያ ድንበር ከተማ ሞያሌ ሁለት ቀበሌ ያላት ሲሆን አንደኛውን ቀበሌ ከተማዋን እኩል ለሁለት በሚከፍለው አውራ መንገድ በስተምእራብ ያለውን ኦሮሚያ ክልል [ክልል 4] ተብሎ የተካለለ ሲሆን በስተምስራቅ ያለውን የከተማዋን ክፍል ክልል 5 ወይም ሶማሌ ክልል ተብሎ መከፈሉ የሚታወቅ ነው።

በነጋዴው ማህበረሰብ ዘንድ በኢ-ፍትሃዊነቱ ብዙዎችን ከስራ ገበታ እያፈናቀለ ያለው አዲሱ የግብር ተመን በሶማሌ፣ በትግራይ፣ በሐረሪና በአፋር ክልሎች እንደ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በአዲስ አበባ ክልሎች እንደተተመነው በኢ-ፍትሃዊነቱ ከነጋዴው ማህበረሰብ አቅም አንጻር ተጋኖ በቅጣት መልክ የተተመነ ሳይሆን በተስተካከለ ተመን ደረጃ የተተመነ በመሆኑ ከፍተኛ ልዩነት ሊታይ ችሏል ሲሉ ያነገገርናቸው ነጋዴዎች ገልጸውልናል።

ከአዲስ አበባ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ስርዓቱ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን እያጠናከሩ ይቃወሙኛል ያላቸውን የአማራውን እና የኦሮሚያን ክልሎች በቀዳሚነት ለመቅጣት የግብር ተመኑን እንደመሳሪያነት እየተጠቀመበት መሆኑን ይገልጹና ዋና ዓላማውም ኢኮኖሚያዊ ጡንቻ አፈርጥመው የሚቃወሙኝን ወገኖች ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን በማንኮታኮት ፍጹም ተገዢ አደርጋቸዋለሁ በሚል እሳቤ እንደሆነ የስርዓቱን ዓድሎዓዊነት በማጣቀስ ይናገራሉ።

በትግራይ፣ ሱማሊያ፣ ሐረሪና አፋር ክልሎች ያሉ ነጋዴዎች በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በደቡብ ክልሎች ያሉ ነጋዴዎች በኢ-ፍትሃዊው የግብር ተመን እንዳልተጎዱ ለማወቅም ተችሏል።