በኬኒያ የምርጫ ውጤት እወጃ በተነሳ አመጽ የሟቾች ቁጥር 24 ደረሰ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ዓርብ ወደ እኩለ ለሊት አቅራቢያ የኬኒያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ የ2017 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ ናቸው ተብሎ ከታወጀ በኋላ በተነሳ አመጽ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 24 መድረሱን ማምሻውን የኬኒያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አሳወቀ።
ዓርብ ከእኩለ ለሊት ጀምሮ በናይሮቢ፣ በኪሱሙ፣ ሚጎሪ፣ ሲያያ እና ሆማ ቤይ በተባሉ ካውንቲዎች በተነሳ ዓመጽ 24 ሰዎች በፖሊስ እንደተገደሉ የተነገረ ሲሆን አድማ በታኝ ፖሊስም ከፍተኛ ግብግብ እያደረገ መሆኑን ተገልጿል።

image

በናይሮቢ የ17 ሰው አስከሬን ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን በኪሱሞ 2 ሰው፣ በሆማ ቤይ 2፣ ሚጎሪ 2 ሰዎች መገደላቸውን ለማወቅ ተችላል።

በናይሮቢ ኪቢራ፣ መዳሬ ከፍተኛ ዓመጽ መነሳቱ የታወቀ ሲሆን አመጸኞቹ የተሸናፊው የናሳ ድርጅት መሪ የራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎች የሆኑ ሲሆን ምክንያቱንም የምርጫ ቦርዱ ውሳኔ ፍትሃዊ አይደለም በሚል ነው።

አርብ እለት ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የ2017 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ ናቸው ተብሎ ሲገለጽ ዋናው ተቀናቃኝ የሆኑት አቶ ራይላ ኦዲንጋ ውጤቱን አልቀበልም ያሉ ሲሆን ምርጫ ቦርድ አጭበርብሯል ሲሉ ተናግረዋል። የተቃዋሚው ውሳኔ የኬኒያን መረጋጋት በማራዘም ዛሬ ለስድስተኛ ቀን አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ስራ ሳይጀምሩ በፍርሃት ዘግተው እንዲውሉ አድርጓቸዋል።