በአማራ ክልል ከሰኞ ጀምሮ የተዘጉ ሱቆች ባለመከፈታቸው የክልሎች የአስተዳደር ሃላፊዎች ጉዳዩ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን እየተናገሩ ነው ተባለ

0

በአማራ ክልል ከሰኞ ጀምሮ ተዘግተዉ የሚገኙ ሱቆችን ለማስከፈት የአገዛዙ አካላት የሚያደርጉትን የማታለል ማግባቢያ ነጋዴዉ ህብረተሰብ ሊቀበለዉ ባለመቻሉ መንግስት ድንጋጤ ዉስጥ መግባቱን የሚደርሱን መረጃዎች እያመለከቱ ነዉ። በወልድያ ዛሬ ነሀሴ 5 ቀን ተጠርቶ የነበረዉ የነጋዴዎች ስብሰባ በነጋዴዉ እምቢተኝነት መበተኑ ሲታወቅ፣ ከነጋዴዎቹ በደረሰን መረጃ መሰረት የሱቆቹ ተዘግቶ መዋል እና ማደር ስጋት ዉስጥ የከተታቸዉ የመንግስት አካላት ከእረቡ እለት ጀምሮ በየነጋዴዎቹ መኖሪያ ሰፈር በመዞር ሱቆቻችሁን ክፈቱ እንጂ የጠየቃችሁት መፍትሄ ይሰጣችዃል፤ ሱቆች የታሸጉባችሁ ነጋዴዎችም ያለቅጣት ይከፈትላችዃል፤ የሚል ማግባቢያን ሲያደርጉ ቢቆዩም፤ ነጋዴዉ የተጨመረዉን ግብር ሙሉ በሙሉ ማንሳታችሁን በማስረጃ ካላረጋገጣችሁልን አንከፍትም ማለቱ ታዉቋል፡፡ ወልድያን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችም  አገዛዙ በአነስተኛ እና በጥቃቅኑ አደራጅቶ እና የኮንቴነር ሱቆችን ሰጥቶ በመነገድ ላይ ለሚገኙ ነጋዴዎች፤ ሱቁ የመንግስት እንጂ የነሱ እንዳልሆነ በአባላቱ እየተነገራቸዉ ከሌሎቹ ጋር የጀመሩትን አድማ የማያቆሙ ከሆነ ሱቆቹ ከነሱ ላይ ተወስደዉ ለሌሎች እንደሚሰጥባቸዉ እያስፈራሩ በግዳጅ እንዲከፍቱ ተደርጓል፡፡ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት በአሁኑ ሰአት በወልድያ ከኮንቴነር ሱቆች ዉጭ  የ”ሀ” እና የ”ለ” ምድብ ግብር ከፋዮችን ጨምሮ ማንኛዉም አይነት የንግድ እንቅስቃሴ  የግብሩን ጭማሪ በመቃወም መዘጋቱን ገልፀዋል።

ይህን ተከትሎ የከተማዉ ከንቲባ እና ሌሎች ባለስልጣናት ለነጋዴዎቹ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ለዛሬ በጠሩት ስብሰባ መሰረት ነጋዴዉ ከማለዳ ጀምሮ በወልድያ  የባህል አዳራሽ በመሰብሰብ መልስ ሲጠባበቅ ለሰአታት ቢቆይም፤ ስብሰባዉን ከጠሩት አካልት መሀከል ማንም  አለመገኘቱን ተናግረዋል። ከነጋዴዎቹ መሀከልም የተመረጡ እና ከ40 እስከ 50 የሚጠጉ ግለሰቦች ወደ ከንቲባዉ ቢሮ በመሄድ ሰብስቧቸዉ መቅረቱ ሀላፊነት የጎደለዉ ተግባር መሆኑን ገልፀዉ መፍትሄ ባስቸኳይ እንዲሰጣቸዉ እንዲሁም የታሰሩ ነጋዴዎችም እንዲፈቱ ጠይቀዋል። ከንቲባዉ ካለመንግስት እዉቅና ሱቆቻችሁን በመዝጋታችሁ ህገወጦች በመሆናቹሁ በመጀመሪያ ሱቃችሁን ከፍታችሁ ህጋዊ ከሆናችሁ በዃላ መነጋገር እንችላለን ብሎ እንዳፌዘባቸዉ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም የግብሩ ጭማሪ የተጣለዉ በ “ሐ” ግብር ከፋዮች ላይ ብቻ ሆኖ ሳለ የ’ሀ” የ “ለ”ምድብ ግብር ከፋዮች በመተባበር ሱቆቻቸዉን መዝጋታቸዉ ሳያንስ ለአቤቱታ አብረዉ መምጣታቸዉ እንደሚያስጠይቃቸዉ በመናግር ለማስፈራራት መሞከሩንም አክለዉ ገልፀዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከፍተኛ ግብር ከፋዮቹ ነጋዴዎች የወንድሞቻችን በደል የኛም በደል ከመሆኑ ባሻገር የግብር ጭማሪዉ ነገም ወደኛ መምጣቱ የማይቀር ስለሆነ ተቃዉሞ ማሰማታችን ተገቢ ነዉ ማለታቸዉ ታዉቋል፡፡ በነጋዴዎቹ ምላሽ የተበሳጨዉ የከተማዉ ከንቲባም ጉዳዩ ከሱ አቅም በላይ መሆኑን ተናግሮ በቀጣይ ሳምንት ዉስጥ በሌላ ስብሰባ እንደሚጠራቸዉ አሳዉቆ ነጋዴዎቹን ከቢሮዉ ማስወጣቱ ታዉቋል፡፤

በተያያዘ ዜናም በራያ፣ ቆቦ፣ ደሴ  እና ኮምቦልቻ ተመሳሳይ የነጋዴዎች አመፅ እየተስተናገደ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል አምቦ እና ጊንጪን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች የነጋዴዎቹ ተቃዉሞ ከግብር ጥያቄ ከፍ ብሎ ወደ አገዛዝ ለዉጥ ጥያቄ እየተለወጠ፤ መንገዶች እየተዘጉ እና ግጭቶች እየተከሰቱ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል። እንዲሁም በሁኔታዉ ከፍተኛ መደናገጥ ዉስጥ የገባዉ የወያኔ ሀርነት ትግራይ ቡድን በየከተማዉ ያሉ ታማኝ አባላቱን ያካተተ አስቸኳይ ስብሰባን እየጠራ መሆኑም ታዉቋል።