የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ አባላት ላለፉት ሶስት ቀናት ሲያካሂዱት የቆየው ግምገማ ዛሬ ተጠናቀቀ

0

ካለፈው ሃሙስ ነሃሴ 4 ቀን ጀምሮ እስከ  ነሃሴ 6 ቀን አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉት ወረዳዎች በሙሉ ሲካሄድ የሰነበተው የካቢኔ አባላት ስብሰባ ትናንት መጠናቀቁን ከውስጥ ምንጮች ለትንሳኤ ዝግጅት ክፍል የተላከ መረጃ አስታወቀ።

የካብኔ አባላቱ የተጠሩበት ግምገማ በከተማው ውስጥ የሚኖሩ ነጋዴዎች የተጣለባቸውን የዕለታዊ ገቢ ግብር ተመን ላይ ተማምነው የሚፈለግባቸውን ዕዳ በወቅቱ እንዲከፍሉ “በቂ የማግባባት ሥራ አልሰራችሁም” የሚል ወቀሳ እንዳዘለና ብዙ ክርክር እንደተካሄደበት ተያይዞ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ግብር ተማኞች በነጋዴዉ ማህበረሰብ ላይ የጣሉት የዕለት ገቢ ግምት እጅግ የተጋነነ በመሆኑ “ከነጋዴዎቹ የመክፈል አቅም በላይ ሆኖአል” በማለት ቅሬታ እየቀረበበት ከመሆኑም በላይ አብዛኞቹ የንግድ ድርጅቶቻቸውን በመዝጋት ተቃውሞ እስከ ማሰማት እንደደረሱ በሰፊው እየተዘገበ እንደሆነ ይታወቃል። የአዲስ አበባ የካቢኔ አባላት በመላው አገሪቱ ተቃውሞ የቀሰቀሰውን የግብር ተመን በምን ተዓምር ማስቆም እንደሚችሉ ሳይነገራቸው በደፈናው “የማግባባት ሥራ ባለመሥራታችሁ የመንግሥት ግብር በወቅቱ ለመሰብሰብ እንዳይቻል አስተዋጽዖ አድርጋችኋል” መባላቸውን በደስታ እንዳልተቀበሉት ስብሰባው ላይ ከተሳተፉ ምንጮች የተላከው መረጃ ይገልጻል።

ግምገማውን ለማካሄድ ከበላይ አካል በተላኩትና ግምገማው ላይ በተሳተፉት የካቢኔ አባላት መካከል መግባባት ባልተቻለበት በዚህ ግምገማ ላይ ህብረተሰቡ ውስጥ እየተሰራጨ ያለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ “በጸረ ህዝቦች የታገዘ ነው” የሚል አጽንኦት እንደተሰጠውና የካቢኔ አባላቱ ይህንን ሴራ ተከታትሎ የማጋለጥ ሃላፊነት እንዳለበት ለማስገንዘብ የተሞከረበት እንደሆነ ታውቋል። አገዛዙ ጸረ ህዝብ ወይም ጸረ ልማት የሚለው አርበኞች ግንቦት 7ን እንደሆነ የገለጹ ምንጮች ለግምገማው ከበላይ አካል የተላኩ ግለሰቦች እንደከዚህ በፊቱ መንፈሰ ጠንካራነትና የመረጋጋት ስሜት ፊታቸው ላይ የሚነበብ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ግምገማውን ሲመሩና ንግግር ሲያደርጉ መሰላቸትና መዳከም በጉልህ ታይቶባቸዋልም ብለዋል። በተለይ ትግሪኛ ተናጋሪ የሆኑ የህወሃት ሰዎች እልህና ድንጋጤ ይታይባቸዋልም ተብሏል። አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖሩ አብዛኛው የህወሃት ካድሬዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በሚያደርጉት ውይይት ጣልቃ በጎንደር በኩል አርበኞች ግንቦት 7 እያካሄደው ያለው እንቅስቃሴ የመሃል አገር ህዝብ ልብ እያሸፈተ እንደሆነ  በማውሳት ዛቻና ፉከራ እንደሚያሰሙ እነዚሁ የካቢኔ አባላት ምንጮች ይናገራሉ።