ህወሃቶች የሟቹን አለቃቸው መለስ ዜናዊን 5ኛ አመት የሙት መታሰቢያ “የሀሳብ ድህነትን ታግሎ ያሸነፈ መሪ” በሚል መሪ ሃሳብ ከትናንትና ጀምሮ እንደሚዘክሩ አዜብ መስፍን አስታወቀች

0

በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በሙስናና የሥልጣን ብልግና የተጨማለቀ የአገዛዝ ሥርዓት በህዝባችን ጫንቃ ላይ ተክሎ ለህልፈት የበቃው የመለስ ዜናዊ 5ኛ የሙት አመት ከትናትና ነሃሴ 6 ቀን 2009 ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የቀድሞ ባለቤቱ አዜብ መስፍን ማስታወቋን ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ ለማወቅ ተችሎአል።

ላለፉት 4 አመታት አንዴ ታላቁ ባለ ራዕይ ሌላ ጊዜ ደግሞ አባይን የደፈረ ታላቁ መሪ በሚል ማቆለጳጰሻ ሲከበር የቆየው የመለስ ዜናዊ ሙት አመት መታሰቢያ በዘንድሮው አመት የሃሳብ ድህነትን ታግሎ ያሸነፈ በሚል መሪ ሃሳብ እንዲከበር መወሰኑ በርካቶችን እያነጋገረ ነው። በከፍተኛ የሃሳብ ድህነት ተቀፍድዶ ለአገር እና ለወገን ዘላቂ ጥቅም የሚበጅ ነገር ማሰብ ተስኖት በከፍተኛ የህዝብ ጥላቻ ወደ ታሪክ ትቢያነት እየወረደ ያለው የህወሃት አገዛዝ እስከዛሬ ከመሪዎቹና  አንጋፋ አባላቱ ያልተላቀቀውን የሃሳብ ድህነት ሟቹ መለስ ዜናዊ ታግሎ እንዳሸነፈ ለማስመሰል መሪ ሃሳብ አድርገው መሰየማቸው የሃሳብ ድህነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ትርጉሙ በትክክል እንዳልገባቸው የሚያመለክት ነው የሚል አስተያየት እየተሰጠ ነው።

ይህንን አስመልክቶ የዝግጅት ክፍላችን ያናገራቸው አንድ የፖለቲካ አቀንቃኝ፤ የአለም ሥልጣኔ መላውን ምድራችንን ባጥለቀለቀበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን እየኖሩ በነጻ ምርጫ ሥነሥርዓት የሚቋቋም መንግሥት ይኑረን በማለት በሠላማዊ መንገድ የሚታገሉ ፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ለማጥፋት አነጣጥሮ ተኳሾችን በህዝብ ላይ ያሠማራና ህጻን ከአዋቂ፣ እናቶችን ከጎልማሶች ሳይለይ በጠራራ ጸሃይ ያስጨፈጨፈ ወንጀለኛ መሪ በየትኛውም ስሌት  የሃሳብ ድህነትን ታግሎ ያሸነፈ ቀርቶ እራሱ ከሃሳብ ድህነት የተላቀቀ ነበር ለማለት እንደሚያዳግት ገልጸዋል።

አክለውም ህወሃት የተሻለ አመለካከትና አስተሳሰብ ያላቸውን አባላቱን በሙሉ በመመንጠር በአንድ አምሳል የተቀረጹ ግለሰቦች ብቻ የቀሩበት ድርጅት በመሆኑ መለስ ዜናዊም ሆነ አሁን በህይወት ሆነው ድርጅቱን በመምራት ላይ የሚገኙ ሰዎች በስብዕናም ሆነ በባህሪ የሚበላለጡ አልነበሩም አሁንም አይደሉም በማለት አገሪቷ ችግር ውስጥ የገባችውም ከመካከላቸው በአስተሳሰብና በአመለካከት የተለየ ደህና ሰው መታጣቱ የፈጠረው ነው ብለዋል።

ዛሬ በህወሃት እስር ቤት ውስጥ የሚማቅቁት እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ ፖለቲከኛው አንዳርጋቸው ጽጌ፣ በቀለ ገርባ፣ ዶር መራራ ጉዲና፣ አንዱአለም አራጌና የመሳሰሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች  ህወሃትን የተጠናወተው የአስተሳሰብ ድህነት ሰለባዎች መሆናቸውን ብዙዎች ይስማሙበታል። ሰሞኑን የህወሃት መሪዎች የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ መሪዎች የሆኑትን ዶር መራራ ጉዲናንና አቶ በቀለ ገርባን በንቀት ለማዋረድ እንደ ወንጀለኛ እጃቸውን በካቴና የፍጥኝ አስሮ የይስሙላ ፍርድ ቤት ማቅረቡን በመቃወም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተቃውሞ ድምጻቸውን እያሰሙ እንደሆነ ይታወቃል።

የሙስና እመቤት የሚል ቅጽል ስም የተሰጣት የመለስ ዜናዊ  ሚስት አዜብ መስፍን እንዲህ አይነት ሥርዓት አገሪቱ ላይ ተክሎ የሄደውን ባልዋን የሞት መታሰቢያ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር በትናንትናው ዕለት መግለጫ መስጠቷን የህወሃት ልሳን የሆነው ፋና ብሮዲካስቲንግ ዘግቧል።