ብአዴን በአቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ በኩል የጠራዉ ስብሰባ ያለ ዉጤት መበተኑ ታወቀ

አባይ ሚዲያ ዜና
ናትናኤል ኃይለማርያም

አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ ነሐሴ 7 2017 በጠሩት ስብሰባ ላይ ከፍተኛ አመራሮች፣ የባህር ዳር ከተማ ከንቲባና አመራሮች፣ የአድማ በታኝ ፖሊስ አመራሮች፣ የክልል ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች፣ የመከላከያ እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኃላፊዎች በዚሁ በተጠራዉ ስብሰባ ላይ መገኘታቸዉ ታዉቋል።

የስብሰባዉ ዋና አጀንዳ ሆኖ ከቀረበዉ አበይት ርዕሶች ዋና ዋናዎቹ በአማራ ክልል ስለ አለዉ የጸጥታና ቁጥጥር አካኼድ፣ ከግብር ጋር ተያይዞ ሱቃቸዉን በአድማ ዘግተዉ ስለነበሩ ባለ ሐብቶች እና ከዚሁ ከግብር አድማ ጋር ተያይዞ በተነሳዉ ችግር በየማጎሪያ ቤት ታስረዉ ስለሚገኙት ኢትዮጵያውያኖች የሚል እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል።

በዚህ ስብሰባ ላይ አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ የጸጥታዉ ጉዳይ በጣም አስጊና ከቁጥጥር ዉጪ እንድሆነ ይስተዋላል በማለት በዚህም ምክንያት በመንግስት እና በሕዝቡ መኻከል ያለመተማመን ችግሮችም እየተስተዋሉ እንደሆነ አፅንኦት በመስጠት ከገለጹ በኋላ ለጸጥታዉ ዘርፍም ከበቂ በላይ በጀት የተመደበ ቢሆንም ፀረ ሰላም ኃይሎችን ቦንብ ከመጣል ሲያስቆም እንዳልታየ ገልጸዋል።

አያይዘዉም ከጸጥታዉ ጋር በተያያዘ የተቋቋሙት ኬላዎች በሙሉ ምንም አይነት ዉጤት እያመጡ እንዳልሆነ የጠቀሱት አቶ ገዱ አሁን ባለዉ ሁኔታ ጸጥታዉ ከቀጠለ ለመቆጣጠር እጅግ አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልጸዉ በተከታታይ የቦንብ ጥቃቶች መፈፀማቸው በነዋሪውና በመንግስት መኻከል ያለመተማመንና በጥርጣሬ አይን እንዲተያዩ ያደርጋቸዋል ሲሉም ተደምጠዋል።

የመከላከያና የብሔራዊ መረጃ ኃላፊዎችም ለችግሩ መባባስ የፖለቲካው አመራርን ተጠያቂ ለማድረግ የሞከሩ ሲሆን የፖለቲካዉ አመራሮችም ችግሩን ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በማያያዝ እና በአዋጁም መሠረት በጀት ከመመደብ ዉጪ ምንም አይነት ሥራ ሊያሠራቸዉ እንዳልቻለ ጠቁመዉ ለኮማንድ ፖስቱ ታዛዥ ሆነዉ የቆዩ መሆናቸዉንም ገልጸዋል።  የጸጥታዉ ጉዳይ የሚመለከተዉ የብሔራዊ መረጃና ደህንነቱ መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም።

የመንግስት ተቋማት የሆኑት መብራት ኃይል የቴሌኮሚዩኒኬሽን መስሪያ ቤትና፣ የውሃ ልማት ቆጣሪዎችን ማንበብ አለመቻላቸው በተለይ በቴሌኮሚዩኒኬሽን የተንቀሳቃሽ ስልክ የካርድ ሽያጭ ሙሉ በሙሉ በሚያስችል ደረጃ መሸጥ ቆሟል ማለት ይቻላል።

በዚህ ከቀጠለ ባለንብረቶች ሊከሱ ወይም ሁኔታውን ወደ አመፅ ሊቀይሩት ይችላሉ የሚል ፍራቻ እንዳላቸዉም ተሰብሳቢዎቹ ስጋታቸዉን መግለጻቸዉ ታዉቋል። በሌላም በኩል ከአድማው ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎች ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውና መፍትሔ አለመሰጠቱ ከፍተኛ ችግር መሆኑም በዚሁ ስብሰባ ከቀረቡት አጀንዳዎች እንደ ሌሎች ሁሉ ስምምነት ያልተደረሰበት እንደነበር ታዉቋል።

ስብሰባዉ በመጨረሻም ያለምንም ስምምነት መበተኑ ከስፍራዉ በደረሰን መረጃ ለመረዳት ተችሏል።