የዝምባቡዌ ቀዳማዊ እመቤት በደቡብ አፍሪካ ያለመከሰስ መብት ሊሰጣቸው ነው ተባለ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በደቡብ አፍሪካ በተከፈተባቸው የድብደባ ክስ ከሀገር እንዳይወጡ የታገዱት የዝምባቡዌ ቀዳማዊ እመቤት ግሬስ ሙጋቤ በዙማ መንግስት ዲፕሎማሲያዊ ያለመከሰስ መብት ሊሰጣቸው ነው ሲል ሮይተርስ የዘገበ ሲሆን የመንግስትን ውሳኔ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ተቃዋሚዎች ክፉኛ እንደተቃወሙት ለማወቅ ተችላል።

የ20 ዓመቷ ገብሬላ ኤንጅልስ የተባለች ወጣት ደቡብ አፍሪካዊት የዝምባቡዌውን ፕሬዚዳንት ሮበት ሙጋቤ ባለቤት ግሬስ ሙጋቤ በኤልክትሪክ ገመድ ገርፈውኛል ስትል ለደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በመክሰሷ ቀደማዊት እመቤቷ ከጆሓንስበርግ እንዳይወጡ በፖሊስ ታግደው ያሉ መሆናቸው ታውቋል።

የደቡብ አፍሪካው ፖሊስም ለቀዳማዊቷ እመቤት የተለየ እንክብካቤን ሳያደርግ ለፍርድ እንደሚያቀርባቸው በመወሰኑ የዙማ መንግስት ከሙጋቤ ጋር የዲፕሎማሲያዊ ግጭት ይፈጠርብኛል በሚል ስጋት በጉዳዩ ጣልቃ በመግባት የ52 ዓመቷን ተከሳሽ ግሬስ ሙጋቤን ያለመከሰስ ዲፕሎማቲካዊ መብት [Immunity] በመስጠት ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን መንገድ ለማመቻቸት መወሰኑን ነው ሮይተርስ የዘገበው።

ለስብሰባ ወደ ደቡብ አፍሪካ የተጓዙት የ52 ዓመቷ ግሬስ ሙጋቤ በብዙዎች ዘንድ የ93 ዓመቱን ፕሬዚዳንት ሙጋቤን ስልጣን ወራሽ ተደርገው የሚታዩት፣ ልጃቸውን ለማየት ወዳረፉበት ሆቴል የሄደችውን የ20 ዓመቷን ወጣት በኤልክትሪክ ገመድ እንደገረፏት ተገልጿል። በዚህም ምክንያት ፖሊስ ለፍርድ ለማቅረብ እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት የፕሪቶሪያ ባለስልጣናት ከዝምባቡዌዋ ሙጋቤ ጋር ከመጋጨት ቀዳማዊ እመቤቲቱን በነጻ ለማሰናበት በመወሰን መንቀሳቀስ የጀመረ ሲሆን የገጠመው ተቃውሞም ቀላል ነው ተብሎ የሚታለፍ አልሆነለትም።

በፖሊስ ከሀገር እንዳይወጡ የታገዱት ወ/ሮ ግሬስ ሙጋቤ ለግዜው ድምጻቸውን አጥፍተው ማድባትን የመረጡ ይመስል ሲናገሩም ሆነ መልስ ሲሰጡ እይታይም።