ከነሀሴ 17- 21 ድረስ በመላ ኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች የትራንስፖርት አገልግሎት ይቆማል ተባለ፣ ጎጃም በአድማ ላይ ነው

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ከፊታችን እረቡእ ነሀሴ 17 ቀን እስከ እሁድ ነሀሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም በመላ ኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ክልሎች ያሉ አውራ መንገዶች ለባጃጅ፣ ቀላልና ከባድ የህዝብ ማመላለሻዎችና የጭነት መኪናዎች ሁሉ መንገዱ ዝግ መሆኑን የስራ ማቆም አድማ አስተባባሪዎች የገለጹ ሲሆን በተጠቀሱት ቀናት አድማውን ተላልፈው ለሚገኙ አሽከርካሪዎች ለሚደርስባቸው ጉዳት ሃላፊነቱ የራሳቸው ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በሀገር አቀፋ የትራንስፖርት የስራ ማቆም አድማ አስተባባሪዎች ማንኛውም አሽከርካሪ ከእረቡእ እስከ እሁድ ባሉት 5 ቀናት ውስጥ በስራ ማቆም አድማ ለትራፊክ ዝግ ይሆናሉ ያላቸውን መንገዶች በዝርዝር ያስታወቁ ሲሆን አድማውን ጥሶ በተገኘ ማንኛውም አሽከርካሪ ላይ እርምጃ እንደሚወሰድበት በአጽንኦት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በስርዓቱ ፈጻሚነት እየተደመጡ ያሉ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች በተለይም ከየእስር ቤቶቹ የሚደመጡ ሰቆቃዎች የብዙዎችን ልብ ያሸበረና ብሎም ያስጨነቀ ሲሆን በዓመታዊ ግብር ስም በነጋዴው ማህበረሰብ ላይ ከተተመነው ኢ-ፍትሃዊው የግብር ተመን ሁኔታን ዜጎች በተለያየ መንገድ ተቃውሞዋቸውን እንዲገልጹ እንዳደረገ የሚታወቅ ሲሆን የስራ ማቆም አድማም ተቃውሞን ለመግለጽ ከሚጠቀሙበት መንገዶች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ለማወቅ ተችላል።

እንደ ሀገር አቀፉ የትራንስፖርት አድማ አስተባባሪዎች መግለጫ ከፊታችን እረቡእ ነሀሴ 17 ቀን እስከ እሁድ ነሀሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ ከአዲስ አበባ ተነስተው በሚሄዱት አራቱም ማእዘኖች ማለትም በምስራቅ ከአዲስ አበባ እስከ ሐረር፣ በደቡብ ከአዲስ አበባ እስከ ሞያሌ እና በወሊሶ በኩል እስከ ጂማና እንዲሁም በምእራብ ከአዲስ አበባ እስከ ደምቢዶሎ በሚወስደው አውራ መንገዶች ለትራፊክ ዝግ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሰሜን በኩልም ከአዲስ አበባ ተነስቶ ጎጃምን እና ባህር ዳርን አቋርጦ እስከ ጎንደር፣ በሰሜን ምስራቅም በኩል ከአዲስ አበባ ተነስቶ በደብረ ብርሃን አቋርጦ ወደ ወሎ በሚወስደው እስከ ወሎ ድረስ ያለው አውራ መንገድ ለትራፊክ ተዘግቶ ለአምስት ቀናት መቆየት አለበት ሲሉ አስረድተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጎጃም ደብረ ኤሊያስ እየተካሄደ ያለው የስራ ማቆም አድማ ለሁለተኛ ቀን ቅዳሜም ተጠናክሮ መቀጠሉን የደረሰን መረጃ የሚያመለክት ሲሆን የስራ ማቆም አድማውም የተጫነባቸውን ኢ-ፍትሃዊ የንግድ ተመን በመቃወም እንደሆነ ገልጸዋል።