በአብዛኛው የአገራችን ክፍል አምና ተካሂዶ በነበረው ህዝባዊ እምቢተኝነት ህወሃት/ኢህአደግ እንደ መንግሥት የመቀጠል አደጋ ውስጥ ወድቆ እንደነበር አንድ ከፍተኛ የኢህአደግ ባለሥልጣን አጋለጠ

0

በኦሮሚያና በአማራ ክልል አምና በዚህን ወቅት ተቀስቅሶ በነበረው ህዝባዊ እምቢተኝነት አገዛዙ መያዣ መጨበጫ አጥቶ ከመፈረካከስ አደጋ ጫፍ ላይ ደርሶ እንደነበር ያጋለጠው ሰሞኑን በአዳማ ከተማ ተካሂዶ በሰነበተው የኦሮሚያ ክልል የ2009 በጀት ዓመት ሥራ አፈጻጸም እና የ2010 ዕቅድ ለመገምገም ተጠርቶ የነበረውን የግምገማ መድረክ የመራው የክልሉ ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ ነው።

ከህወሃት ባለሥልጣናት እስከዛሬ ተሰምቶ በማይታወቅ ግልጽነትና ድፍረት በአዳማ የኦሮሚያ ክልል ስብሰባ ላይ አገዛዙን ገጥሞት የነበረውን መደናገጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ያደረገው ለማ መገርሳ በተለይ በሁለቱ ክልሎች የሚኖረው ህዝብ ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስችል መነሣሣት አገዛዙ ላይ አምጾ እንደነበር እና በዚህም የተነሳ እርሱን ጨምሮ አብዛኛው ከፍተኛ አመራር ‹‹ነገ ምን ይውጠናል? ይህ መንግስት ይቀጥላል ወይስ አይቀጥልም? ድርጅታችን ይፈርሳል ወይስ ይቀጥላል? እውነት ከዚህ ጨለማ መውጣት እንችላለን ወይ?›› በማለት ተስፋ የቆረጡበት ጊዜ ውስጥ እንደነበሩ ገልጿል፡፡

በመቀጠልም “በአገዛዙ ላይ እጅግ የተማረረው ህዝብ በላያችን ላይ የድንጋይ ናዳ ሲያዘንብብን፤ መኖሪያ ቤቶቻችን እና ቢሮዎቻችን  ላያችን ላይ በእሳት ሲያቃጥል ሌላው ቀርቶ ይህ 3 እና 4 ሚሊዮን የምንላቸው አባላቶቻችን  ሳይቀሩ ተስፋ ቆርጠው በመንፈስና በሥጋ መለየት ብቻ ሳይሆን ትጥቃቸውንም ፈተው ነበር” ብሏል ለማ መገርሳ በአዳማው የሰሞኑ ስብሰባ።

“አምና በዚህች ወቅት፣ በዚህች ሰዓት፣ በዚህች ደቂቃ ምን ውስጥ ነበርን? ዛሬስ የት ነን?”  በማለት በስብሰባው ላይ የታደሙትን የክልሉን አመራሮችና ካድሬዎች  የጠየቀው ለማ መገርሣ ከዛ ጨለማ ለመውጣት  እርሱና አለቆቹ ምን አይነት ስትራቴጂ ቀይሰው እንደተንቀሳቀሱ፤ አካሄዳቸውንና  አሰራራቸውን አስተካክለው አመራሩን ብቻ ሳይሆን በሀገር ደረጃም ጭምር ተስፋ አስቆራጭ የነበረውን ሁኔታ ለመለወጥ  ተስፋ ሳይቆርጡ እንዴት ታግለው ማንም ያልጨበጠውን እሳት ሳይፈሩ ጨብጠው በመስራት የነበረውን ሁኔታ መቀልበስ እንደቻሉና ተስፋ ሰጪ ሁኔታ እና አበረታች ለውጥ እንዳመጡ አስረድቶአል።

ለማ መገርሳ በክልል ፕሬዝዳንትነት የሚያገለግለው አገዛዝ ህልውና ጥያቄ ውስጥ በገባበትና እንደ ሥርዓት ለመቀጠል አጣብቂኝ ውስጥ በነበረበት ወቅት ሲትራቴጂ ነድፈውና አካሄዳቸውን አስተካክለው እጅግ ተስፋ አስቆራጭ የሆነውን ሁኔታ ቀይረናል በማለት ስብሰባው ላይ የተናገረው፣ ህወሃት የሲቪል አስተዳደሩን ሥልጣን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቀምቶ አገሪቱን በወታደራዊ ቀጠናዎች በመከፋፈል በጉልበት ህዝባዊ እምቢተኝነቱን ለጊዜው ማቀዝቀዝ የቻለበትን ሂደትና ጥልቅ ተሃድሶ በማለት በወሰደው እርምጃ እርሱንና መሰሎቹን ወደ ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ያመጣውን ለመግለጽ እንደሆነ ከንግግሩ ለመረዳት ተችሏል።

በህወሃት ደህንነት መሥሪያ ቤት ውስጥ ተኮትኩቶ ያደገው ለማ መገርሣ በሳሞራ ዩኑስ ባላንጣነት መቆሙ ከሚነገርለት የጌታቸው አሰፋ ቡድን ጋር  የቀረበ ግንኙነት እንዳለው ይነገርለታል። በዚህም የተነሳ ህወሃት ያለ የሌለ አቅሙን ሰሜን ውስጥ ወደሚደረገው ህዝባዊ አመጽ ለማዞር ይችል ዘንድ ኦሮሚያ ውስጥ መረጋጋት እንዲፈጥር ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የህዝቡን ብሶትና ምሬት እየተናገረ የለውጥ ሃዋሪያ መስሎ እንዲታይ በፈለገው አቅጣጫ እንዲንቀሳቀስ የተለቀቀ ሰው እንደሆነ ለደህንነት መሥሪያቤቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ይገልጻሉ።

ህወሃት አካሂጃለሁ በሚለው ተሃድሶ ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሆኖ ከተሾመ ወዲህ ከኦሮሚያ ጋር በሚዋሰኑ ክልሎች ጋር ደም አፋሳሽ የሆኑ የድንበር ግጭቶች እየተነሱ በርካታ የኦሮሞና የአጎራባች ክልሎች ተወላጆች ህይወት እየተቀጠፈ መሆኑ ታውቋል። በትናንትናው ዕለት የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮ የክልሉን ነዋሪዎች ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው በሱማሌና በኦሮሚያ ድንበሮች ላይ ሰሞኑን ተባብሶ በቀጠለው የድንበር ግጭት የሱማሌ ክልል ልዩ የጸጥታ ጥበቃ ታጣቂዎች በህወሃት ወታደሮች በመታገዝ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ከፍተኛ ግድያ እየፈጸሙ መሆናቸውን ዘግቧል። ለማ መገርሣና አዲሱ የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር ይህንን ግዲያ ለማስቆም እስከዛሬ በግልጽ የወሰዱት እርምጃ እንደሌለ የአካባቢው ህዝብ በምሬት ይናገራል።

በኦሮሚያ አካባቢ ህዝቡን ተዘዋውሮ በማነጋገር አስተማማኝ ሠላምና መረጋጋት እንደፈጠረ በአዳማው የሰሞኑ ስብሰባ ላይ በእርግጠኝነት የተናገረው ለማ መገርሣ በመጪው የኢትዮጵያ አዲስ አመት ለአንድ ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመክፈት ክልሉ እየሠራ መሆኑን በመግለጽ ህወሃት 27 አመት ሙሉ ህዝቡን በተስፋ አንጠልጥሎ ለመግዛት እያደረገ ያለውን ፕሮፖጋንዳ አጠናክሮአል።

የኦሮሚያ ወጣቶች እየጠየቁት ያለው የሥርዓት ለውጥ መሆኑን ያልተረዳው ለማ መገርሣ በኦሮሞነታቸው ምክንያት ታሥረው እስር ቤት ከተወረወሩ በኋላ አሰቃቂ የሆነ ድብደባና ማሰቃየት በህወሃት ገራፊዎች እየተፈጸመባቸው በለጋ ዕድሜያቸው አካለ ጎዶሎ ስለሆኑ ሺዎች ወይም የአገሪቱን ዕስር ቤት በብዛት ከማጥለቅለቃቸው የተነሣ አዲስ አበባ የሚገኙ ዕስር ቤቶች ሳይቀሩ ኦሮሚኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሆኗል ስለተባለላቸው በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ እስረኞች አንድም ቀን ሲናገር ተሰምቶ አያውቅም።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና የኦሮሚያ ክልልን በወታደራዊ  አስተዳደር ሥር በማስገባት በተፈጸመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ለጊዜው ጋብ ብሎ የነበረውን ህዝባዊ ተቃውሞ የሠላም መስፈን ምልክት አድርገው እራሳቸውን በማሞኘት ላይ ያሉ ለማ መገርሣና አበሮቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞች ተቀስቅሶ ወደ መላው አገሪቱ እየተሰራጨ ያለውን እምቢተኝነት ተወጥተነዋል ወደ አሉት ስጋት የሚመልሳቸው መሆኑን ገና እንዳልተረዱት ከሚሰጡት መግለጫ ለመረዳት ተችሎአል።

የህወሃት ተሃድሶ በክልሉና በአገሪቱ ያመጣውን አስተማማኝ ሠላምና መረጋጋት ለማ መገርሳ ተናግሮ ሳምንት ሳይሞላው የኦሮሞ ወጣቶች ለ5 ቀናት የሚዘልቅ የሥራ ማቆም አድማ በመላው አገሪቱ እንዲደረግ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ኢሳት በትናንትው ዐርብ ዝግጅቱ ይፋ አድርጓል። በዚህ አጋጣሚ የትንሳኤ ሬዲዮ የኦሮሚያ ወጣቶች የጠሩትን ይህንን የሥራ ማቆም አድማ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ዜጎች እንዲቀላቀሉት ጥሪውን  ያቀርባል።