ዘረኝነት እና ስሜታዊነት የህወሃት አገዛዝን አጣብቂኝ ችግሮች ውስጥ እንደከተተው የአሜሪካ አምባሳደር ሆኖ የተሾመው ካሳ ተክለብርሃን አስታወቀ

0

ካሳ ተክለብርሃን የሟቹን መለስ ዜናዊ 5ኛ አመት መታሰቢያ አስመልክቶ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባካሄደው ቃለ መጠይቅ የመለስን ውርሶች ከማስቀጠል አኳያ “ከስሜትና ከዘረኝነት የጸዳ አስተሳሰቦችን ከሚዛናዊነት ጋር ሰንቆ መጓዝ እና ህብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰርጽ ማድረግ ይገባል” በማለት ጀምሮ ህወሃት ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ዕለት ጀምሮ በአገሪቱ እና እራሱ ጠፍጥፎ በሰራቸው የኢህአደግ አባል ድርጅቶች መካከል ሲተገብረው የኖረው የበላይነት የድርጅቱን ህልውና ምን ያህል እንደሸረሸረውና የህዝብ ጠላትነት እንደፈጠረበት በደብሳሳው ገለጸ።

መላው አገሪቱን ያዳረሰውn ህዝባዊ እምቢተኝነት ተከትሎ ህወሃት አካሂጃለው ባለው ጥልቅ ተሀድሶው ወቅት በነበረው ግምገማ “አመራሩ ህዝባዊነት እና ጥርት ያለ የዓላማ ፅናትን ከመላበስ አኳያ ክፍተቱ በግልፅ ታይቷል”  የሚለው ካሳ ተክለብርሃን “ከዚያ ወዲህ ድርጅቱ ውስጥ የጎራ እና የሰልፍ መደበላለቆች እየታዩ በመሆኑ ከስሜትና ከዘረኝነት የፀዳ አስተሳሰቦችን በማስረፅ ሰልፍን ማስተካከል ይገባል” በማለት አንጋፋዎቹ እና በከፍተኛ ሌብነት ወንጀል የተዘፈቁት  የህወሃት አለቆቹ በርሱና በመሰሎቹ ላይ ያነጣጠሩትን በሙስና ወንጀል ወደ ዘብጢያ መወርወር እርምጃ እንዲገቱ መልዕክቱን አስተላልፎአል።

በቃለ መጠይቁ ውስጥ መለስ ዜናዊ በህይወት ቢኖር ኖሮ አሁን አገዛዙን የገጠመው ፈተናና ችግር በወቅቱ መፍትሄ ያገኝ ነበር የሚለውን የአንዳንድ ወገኖች አስተያየት እንደማይጋራ ፈራ ተባ እያለ ለመግለጽ የሞከረው ካሳ ተክለብርሃን መለስ በህይወት በነበረበት ወቅትም ተመሳሳይ ችግር ገጥሞ ድርጅቱ ተሃድሶ እንዳደረገ በመግለጽ በሞት የተለየው መለስ ዜናዊ ከአሁን በኋላ ስለማይመለስ “ጓድ መለስ ቢኖር” እያሉ እና ነገሮችን እርሱ በህይወት በነበረበት ወቅት ከነበረው ጋር እያወዳደሩ መፍትሄ ማምጣት እንደማይቻል አውቀው እራሳቸውን ከሙት መንፈስ እስረኛነት እንዲያላቅቁና ተግባራዊ መፍትሄ እንዲፈልጉ የበኩሉን ጥሪ አቅርቧል።

ካሳ ተክለ ብርሃን በከፍተኛ ሙስና ከተዘፈቁና በሃብት ዘረፋ በብርሃን ፍጥነት ከከበሩ የወያኔ/ኢህአደግ ነባር ታጋዮች አንዱ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከአገውና ከትግራይ ብሄረሰብ የተወለደው ካሳ ተክለብርሃን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳይገባ ከአዜብ መስፍን ጋር ህወሃት ካቋቋመው የስቪል ኮሌጅ ተመርቆ በገንዘብ ሃይል የሁለተኛ ድግሪ ባለቤት ከሆኑት ሰዎች እንዱ እንደሆነም ይታወቃል።