ከግማሽ በላይ የአገሪቱን ዜጎች ለከፍተኛ የሥራ አጥነት ችግር የዳረገው የህወሃት አገዛዝ ለ 8.4 ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ ዕድል እከፍታለሁ የሚል የማዘናጊያ ፕሮፖጋንዳ መጀመሩ ታወቀ

0

ህወሃት በአዲስ መልክ የጀመረው ይህ አዲስ የቅስቀሳና ፕሮፖጋንዳ ሥራ ይፋ የሆነው  ነሃሴ 13  ቀን 2009 ሃዋሳ ከተማ ላይ በተካሄደው የፌደራል ምግብ ዋስትናና ስራ እድል ፈጠራ ኤጄንሲ ዘርፍ  የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ሃገር አቀፍ ፎረም ስብሰባ  ላይ ነው፡፡

የኤጄንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር  በቀለ መንግስቱን ገልጾ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደ ዘገበው ህብረተሰባችን በህወሃት  አገዛዙ ላይ ያለውን ተቃውሞና ጥላቻ ያረግብልኛል ብሎ ለሁለተኛ ጊዜ እያካሄድኩት ነው በሚለው   የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን 8.4 ሚሊዮን ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ የተያዘው አቅጣጫ በአግባቡ እየተተገበረ ነው ተብሏል።

በእቅዱ መሰረት ባለፉት ሁለት አመታት በየአመቱ በአማካይ 1.6 ሚሊዩን ዜጎችን ወደ ስራ ማስገባት ተችሏል  ያለው የኤጄንሲው ዳይሬክተር በቀለ መንግስቱ ከ2008 ጀምሮ ከ3 ሚሊዮን የሚበልጡ ወጣቶች የእድሉ ተጠቃሚ እንደሆኑ ገልጿል። በተያዘው የ2010 በጀት ዕቅድ 2 ሚሊዮን ለሚሆኑ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንቅስቃሴ መጀመሩንም አክሎ ገልጿል።

ህወሃት የመንግሥት ሥልጣን ከተቆጣጠረበት የመጀመሪያው አመት ጀምሮ በአሥር አመት ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያን ህዝብ በሙሉ በቀን ሶስት ጊዜ እንዲበላ አደርገዋለሁ የሚል ፕሮፖጋንዳ በመንዛት በርካታ ህዝብ አሜን ብሎ አንዲገዛለትና በተስፋ እንዲጠባበቀው በማድረግ ሥልጣን ላይ ለመደላደል እድል እንዳገኘ በስፋት ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል።

አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሃት ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊት ቢያንስ በቀን ሁለትና ከዚያም በላይ በልቶ ለማደር ችግር ያልነበረበት ህብረተሰብ እንደነበረ መረጃዎች ይመሰክራሉ። ሆኖም ባለፉት 27 የህወሃት አገዛዝ ዘመን ከነበረበት ደረጃ ቁልቁል ወርዶ ከቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ ለቅሞ እስከ መብላት የደረሱ ዜጎች የታዩበትና በዋና ከተማው በአዲስ አበባ ከሆቴል የሚወጣ የምግብ ትርፍራፊ በጉርሻ እየተሻሙት ህይወታቸውን ለማቆየት የቻሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል። ከዚህ አዋራጅ ኑሮ ለመላቀቅ ሲሉ የዩኒቬርስቲ ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ በግርድናና በአሽከርነት ተቀጥረው ለመኖር ወደ አረብ አገሮች የተሰደዱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የተመዘገቡ እንደሆነም ይታወቃል። በእግርና በባህር ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ሲሞክሩ ባህር ውስጥ ሰጥመው የሞቱና በጨካኞች ካራ እንደ እንስሳ የታረዱ ዜጎቻችንን ያየንበትም ኢኮኖሚው በየአመቱ 10 እና 11 በመቶ አድጎአል እየተባለ በአገር ሃብት ዘረፋ የደለቡ የህወሃት መሪዎች በሚያሾፉብን የታሪክ ወቅት እንደሆነ  ብዙዎቻችን የምናስታውሰው በከፍተኛ ህመም ነው።

ይህ ስቃይና መከራ አፍጦ የወጣ የየዕለት ኑሮአችን ገጠመኝ ሆኖ ሳለ ከሰሞኑ ጀምሮ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጠራል የሚለው የህወሃት ቅስቀሳና ፕሮፖጋንዳ ለመታመን ቀርቶ የማንንም ቀልብ ለመሳብ ዕድል የሚያገኝ እንዳልሆነ  ከህዝባችን የተሰወረ አይደለም የሚሉ ብዙ ናቸው።

የህወሃት አገዛዝ ከ45 እስከ 55 በመቶ የሚደርሰውን የአገሪቱን ሥራ አጥ ቁጥር በተለመደው ቁጥር በመጠምዘዝ ስልቱ  ከ16 በመቶ በታች እንደሆነ ሲገልጽ እየተሰማ ነው።