በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ውስጥ የሚፈጸሙ ማሰቃያዎችን ታሳሪዎች እያጋለጡ ነው

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ እስር ቤቶች ውስጥ የሚፈጸሙትን አሰቃቂ የማሰቃያ ተግባሮችን የታሰሩት እሰረኞች ከተለያየ ስፍራ ሆነው ዛሬም እያጋለጡ መሆናቸውን የጀርመን ድምጽ የታሳሪዎችን ቃል ጠቅሶ ዘገበ።

በሀገር ውስጥ ባሉ እስር ቤቶች ከተራው ፖሊስ ጣቢያ ጀምሮ በወንጀል ምርመራ፣ በማእከላዊ እና ብሎም በማረሚያ ቤቶች እንደ ቂሊንጦ፣ ቃሊቲና ዝዋይ እስር ቤቶች ውስጥ ባሉ የፖለቲካ እስረኞች ላይ የሚፈጸመው የማሰቃያ ተግባራት ሰለባ የሆኑት እስረኞች በተንገሸገሸ አገላለጽ ለራዲዮው የገለጹ ሲሆን ድርጊቱንም “በአንድ የሀገር ዜጋ ላይ ቀርቶ በባእድ ጠላት ላይ እንኳን የማይፈጸም ኢ-ሰብዓዊ ጭካኔ ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂውማን ራይትስ ሰዎች [Amnesty International & Human Rights Watch] በኢትዮጵያ መንግስት በእስር ቤቶች ውስጥ የሚፈጸሙትን ኢ-ሰብዓዊ የሆነን የማሰቃያ ተግባራቶችን በተከታታይ በሚያወጧቸው ዓመታዊና ወርሃዊ መግለጫዎች ላይ እየገለጹት ያለ ገሀዳዊ ተግባር መሆኑ ይታወቃል።

በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ በህወሃቶች 84 ተብሎ በሚጠራው የጨለማ ክፍል ለዓመት ሲሰቃይ የነበረና ዛሬ በስደት ያለው ቤኛ ገመዳ የደረሰበትን “ያልሰራሁትን ሰርቻለሁ ብዬ እንዳምን በኤሌክትሪክ ገመድ በሚያሰቅቅ ሁኔታ ተገርፌያለሁ፣ የእግር ጣት ጥፍሮቼን እየነቀሉ አሰቃይተውኛል፣ ከለሊቱ ሰባት ሰዓት እስከ ንጋቱ አስራ አንድ ሰዓት አራት መርማሪዎች እየተፈራረቁ ማንነቴን እስክጠላና ሞት እስከምመኝ ድረስ አሰቃይተውኛል” ሲል ይናገራል።

በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ውስጥ የሚፈጸሙትን አሰቃቂ ተግባራትን ቤኛ ገመዳ በመግለጽ የመጀመሪያም ሆነ የመጨረሻው እንዳልሆነ ካለን ተጨባጭ ማስረጃዎች አንጻር መናገር ይቻላል።

በጎንደር እስር ቤት ለሁለት ዓመታት ያህል ሽፍታና ሌባ ታደራጃለህ በሚል ክስ ተጠርጥሮ ታስሮ የነበረው ወገኑ ማስረሻ በአዲስ አበባው ማእከላዊ እስር ቤት ከተሰቃየው ቤኛ ገመዳን በሚጋራ መልኩ የደረሰበትን “መርማሪዎቹ እኔ የአግ7 እና በጎንደር አከባቢ የሚንቀሳቀሱትን ሽፍቶች አደራጅቻለሁ ብዬ እንዳምን እራሴን እስክስት አሰቃቂ ድብደባና ግርፋቶች ተፈጽሞብኛል” ሲል ተናግሯል።

ቤኛ ገመዳ በኦ.ነ.ግ ተጠርጥሮ ከጋምቤላ ተይዞ በማእከላዊና ቂሊንጦ ከ2011-2015 የተሰቃየ እስረኛ ሲሆን የጎንደር ሰሜን አርማጭሆ ተወላጅ የሆነው ወገኑ ማስረሻም ከሁለት አሰቃቂ የእስር ዓመታት በኋላ ሲፈታ ትዳሩ ፈርሶና ልጆቹን አጥቶ ዛሬ በጎንደር ከህዝቡ ጋር በአግባቡ መግባባት በማይችልበት ደረጃ ተገልሎ ለመኖር የተገደደ ሰው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ከሰሜን ጎንደር ሳንወጣ፣ በወልቃይት የማንነት ጥያቄ ዙሪያ ከ7 ዓመት በላይ መጀመሪያ በጎንደር እስር ቤት ቀጥሎም በአዲስ አበባው ማእከላዊ ምርመራና በቂሊንጦ የተሰቃዩ በርካታ ተጠርጣሪዎች በእስር ቆይታቸው የደረሰባቸውን አካላዊና አእምሮአዊ ጠባሳን ዛሬም በሚያሳቅቅ ሁኔታ ላይ ሆነው ገልጸዋል። ድብደባ፣ የተለያዩ የማሰቃያ ተግባራቶች፣ ክብርና ሞራል ነክ ተግባራት እንደተፈጸሙባቸው ሳይሸሽጉ ገልጸዋል።

ወጣቱ እስረኛና ከወራቶች በፊት ለህክምና ወደ አሜሪካ የተጓዘው ሀብታሙ አያሌው የሁለት ዓመት አሰቃቂ የማእከላዊ ቆይታውን ምስክረነት ቃል ለቪ.ኦ.ኤ ቀጥሎም ለተለያዩ ዜና ጣቢያዎች ይፋ ካደረገ በኋላ በርካታ ታሳሪ የነበሩና ዛሬም በእስር ያሉ እስረኞች በይፋ እየተናገሩ ሲሆን በመንግስት በኩል ተጠያቂነቱን በተመለከተ መልስ ለመስጠት ፍቃደኛ ሆኖ የሚመልስ ሳይሆን በዝምታ ሽሽት ሲያልፈው ፍርድ ቤቶች ደግሞ በተከታታይ ለሚሰሙት የእስረኞቹ አቤቱታ መልስ ባለመስጠት ዝምታ የሚያልፉት ክስተት እንደሆነም ማወቅ ተችሏል።

አሰቃቂዎቹ የእስር ቤት ማሰቃያ ታሪኮች በፖሊስ ጣቢያ፣ በወንጀል ምርመራና በማእከላዊ ብቻ ተወሰኖ የቀረ ሳይሆን ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ደረጃ ላይ ያለና ብሎም ፍርደኞች የሆኑ እስረኞች ቆይታ በሚያደርጉበት የቃሊቲ፣ የቂሊንጦ፣ የዝዋይና የተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ውስጥም በተመሳሳይ ሁኔታ እየተወሰደ ያለ ድርጊት ሲሆን ማረሚያ ቤቶቹ የፍርድ ቤት ትእዛዝ አክባሪ አለመሆናቸውን ጨምሮ ሁኔታቸውን አስከፊ እንዳደረገው ከእስር ቤት ከሚደመጡት ታሪኮች ማወቅ ይቻላል።

የገዢው ፓርቲ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ከማርቀቅ እስከ ማስጸደቅ ድረስ በመስራት እየተጠቀመበት ያለው የሀገሪቷ ሕገ-መንግስት በማንኛውም ሰው ላይ የጉልበት እርምጃ፣ ድብደባና የማሰቃያ ስልቶችን በመጠቀም ተጠርጣሪን ቃል መቀበል ሕገ-ወጥ ነው ብሎ የደነገገ ቢሆንም መንግስት ግን በእስረኞች ላይ ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን እና ደንብን በመጣስ የሚያደርሰው በደልና ስቃይ እንደቀጠለ መሆኑ ይታወቃል።