ከባሕር ዳር ወደ ነቀምት የሚሄደው አውቶቢስ ቆሟል፣ የኦሮሚያን አድማ ተቀላቅለዋል

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ከነገ ነሀሴ 17 እስከ እሁድ ነሀሴ 21 ቀን 2009 ድረስ በመላው ኦሮሚያ ተግባራዊ በሚሆነው የትራንስፖርት የስራ አድማ ላይ የአማራው ክፍልም አንዳችም የትራንስፖርት አገልግሎታቸውን ወደ ኦሮሚያ ግዛት ባለመለክ አድማውን መቀላቀላቸውን ለማወቅ ተችላል። በባህርዳር አውቶቢስ መነሃሪያ ወደ ነቀምት ለሚሄዱ ተጓዦች “እኛ የስራ አድማ በታወጀበት ክልል መኪኖቻችንን በመላክ ጉዳት እንዲደርስባቸው አንፈልግም” በማለት የተጋዦቹን ትኬት መመለሳቸውን ለመረዳት ተችሏል።

በመላ ኦሮሚያ ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆነው የትራንስፖርት የስራ ማቆም አድማ ላይ በአፍራሽነት አገልግሎት ለመስጠት ተሽከርካሪውን ለሚያሰማራ ማንኛውም ባለሀብት በጀግኖቹ ቄሮዎች ለሚደርስበት ጉዳትና ጥቃት ሃላፊነቱን ባለንብረቱ ይወስዳል ሲሉ የአድማው አስተባባሪዎች መግለጻቸው ይታወቃል።

ይህንንም ተከትሎ ከአማራው ግዛት አንዳችም የትራንስፖርት አግልግሎት ወደ ኦሮሚያ ግዛት ባለመላክ የአድማው ተሳታፊነታቸውን እንደገለጹ እየደረሰን ካለው መረጃ መረዳት ይቻላል።

በኦሮሚያ ግዛት ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው የትራንስፖርት ስራ ማቆም አድማ ከአዲስ አበባ ወደ አራቱም አቅጥጫ በሚያደርሱት አውራ መንገዶች ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን ከአስተባባሪዎቹ መግለጫ ላይ ማወቅ የተቻለ ሲሆን በዚህም መሰረት ከአዲስ አበባ ምእራብ ጊንጪ አምቦ መስመር ላይ እስከ ደንቢዶሎ ድረስ መንገዱ ለትራፊክ ዝግ እንደሆነ ተግልጿል።

ከአዲስ አበባ ደቡብ መስመር ከሞያሌ ተነስቶ ዲላ፣ አዋሳና ሻሸመኔ መስመር ዝግ የሆነ ሲሆን በምስራቅ አዳማ በኩል እስከ ሐረር ብሎም በደቡብ ምእራብ በወሊሶ መስመር ወደ ጂማ የሚያደርሰው መስመር እና በሰሜን በሁለት አቅጣጫ በደብረ ብርሃን እና በፊቼ መስመር ያሉት መንገዶች ሁሉ ለትራፊክ ዝግ መሆናቸውን ገልጸዋል። በኦሮሚያ ግዛት የታወጀውና በአማራውም ግዛት ተቀባይነት ያገኘው የትራንስፖርት የስራ ማቆም አድማ ዋና ምክንያት ከቀናት በፊት በጠ/ሚ/ አቶ ደሳለኝ ሃይለማሪያም 40% በሌቦች የተተመነና የተሳሳተ ተብሎ የተገለጸውን ኢ-ፍትሃዊ የግብር ተመንን በመቃወምና ብሎም በየእስር ቤቶቹ የሚሰቃዩትን የፖለቲካ እስረኞችን ለማስፈታትም እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ጠ/ ሚ/ሩ በሌቦችና በውሽት ሪፖርት የተተመነና 40% የተሳሳተ ያሉትን ኢ-ፍትሃዊውን የግብር ተመን ግን እስከአሁን መሻሩን አለመግለጻቸው ይታወቃል።