በአቶ አግባው ሰጠኝ አካልም ሆነ ህይወት ላይ ለሚደርስ ማንኛውም ጉዳት ገዥው ቡድን ተጠያቂ ነው ተባለ

0

በመላው አገራችን ሕዛባዊ ተቃውሞና ጥያቄ መነሳቱና የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ የዜጎችን ድምፅ በመሳሪያ ኃይል ለማፈን መሞከሩንና በዜጎች መካከል ቅራኔ የመፍጠሩን እኩይ ተግባር እንደትላንትናው ዛሬም ቀጥሎበታል፡፡

ሆኖም ግን ዜጎች የአገዛዙን አፈና በመቋቋም ተቃውሞ እና ጥያቄዎቻቸውን ቀጥለውበታል። ሰማያዊ ፓርቲ ለህዝባዊ ተቃውሞ እና ጥያቄ ሙሉ ድጋፍ የሚሰጥ ሲሆን በዚህም በአመራሩና በአባላቱ ላይ የሚደርሰው እስርና ወከባ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡

ከሕዝብ ጋር በተጣላ ቁጥር እውነተኛ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር እና አባላትን በማሳደድ የሚታወቀው ገዥው ቡድን ከ2007 ዓ.ም ምርጫ በፊት አቶ አግባው ሰጠኝን በማሰርና በነመቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን መዝገብ ክስ ተመስርቶበት ከሁለት ዓመት ከስምንት ወራት እስር በኋላ ነፃ ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ነሐሴ 2008 ዓ.ም በተከሰተው የቂልንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ ምክንያት የሀሰት ክስ ቀርቦበት እስከአሁን እየተሰቃየ ይገኛል፡፡

አቶ አግባው ሰጠኝ ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት ለሕዝብ ነፃነትና ለዜግነት ክብር በቁርጠኝነት ሲታገል የቆየ እውነተኝ ታጋይ ነው፡፡ አቶ አግባው ሰጠኝ የሰማያዊ ፓርቲ መስራች አባል የብሄራዊ ምክር ቤት አባልና የሰሜን ጎንደር አስተባባሪ በመሆን ፓርቲው ከተመሰረተበት ጀምሮ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡

አቶ አግባው ሰጠኝን ነሐሴ 2008 ዓ.ም በተከሰተው የቂልንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ ምክንያት የሀሰት ክስ ቀርቦበት እስከአሁን እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ በዝዋይ፣ በሸዋሮቢት እንዲሁም በተለያዩ ጨለማ ቤቶች እያዘዋወሩ የስቃይ ምርመራ አድርገውበታል፡፡ የእምነት ክህደት ቃሉን በግዳጅ እንዲሰጥ ተደርጎ እጁ እግሩ ጀርባው በግርፋት ቆስሏል፡፡

አሁን ደግሞ የግድያ ዛቻ እየደረሰበትና ህይወቱ ለአደጋ ተጋልጧል፡፡ እሱም “ለሕይወቴ ዋስትና የለኝም” በማለት ለፍርድ ቤት አቤቱታ ያቀረበ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ተገቢውን ምላሽ ሊሰጥ አልቻለም፡፡

አቶ አግባው ሰጠኝ አሁን እየደረሰበት ያለው የግድያ ዛቻ በመንግስት ተቋም ስር እያለ እደመሆኑ መጠን የዚህ ግድያ ፈፃሚ ገዢው መንግስት እደሚሆን ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ በፊት አያሌ ሀቀኛ ታጋዮች ህይወታቸውን ያጡ በመሆኑ ዛሬም በአግባው ላይ እንዳይደገም ሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ ስጋት አድሮበታል፡፡

ስለሆነም ገዥው መንግስት ባፀደቀው ህግ መንግስትና በተቀበላቸው አለም አቀፍ ድንጋጌዎች መሠረት ተጠያቂ እንደሚሆን አውቆ የአቶ አግባው ሰጠኝን ህይወት እንዲታደግ ከወዲሁ እናስጠነቅቃለን።

ኢትዮጵያ በነፃነትና በክብር ለዘላለም ትኖራለች!
ነሐሴ 11 ቀን 2009 ዓ.ም