ተሰርዞ የነበረው የአሜሪካን እና የግብጽ የካይሮ ስብሰባ ተስተካክሎ ተካሄደ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ አማካሪ በሆነው ጃሬድ ኩሽነር መሪነት ወደ ካይሮ የተጓዘው የአሜሪካ ልኡካን ቡድን በግብጽ ውጭ ጉዳይ ም/ር ሰራዥነት ሊያደርግ ያቀደውን ስብሰባ ከተሰረዘበት በኋላ ከፕሬዚዳንት አልሲሲ እና ከራሱ ውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ ጋር ሰብሰባው መካሄዱን የአሜሪካው የዜና ወኪል አሶሺዬትድ ፕሬስ [AP] ዘገበ።

በግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ሳሜ ሹክሪ እና በአሜሪካው ልኡካን መሪ ጃሬድ ኩሽነር መካከል ለረቡእ ጠዋት ታቅዶ የነበረው ስብሰባ በውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ አማካኝነት ተሰርዞ እንደነበረ የታወቀ ሲሆን የዶናልድ ትራምፕ አስተዳዳር በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ባለው ቅሬታ ምክንያት ለግብጽ ሊለቀቅ የታሰበውን በመቶ ሚሊዮን ዶላር እርድታ በመታገዱ ምክንያት የግብጽ መንግስት በአጸፋ የወሰደው እርምጃ እንደሆነ ተገልጿል።

ሆኖም ስብሰባው ተሰርዟል በተባለበት ተመሳሳይ ቀን በጃሬድ ኩሽነር የሚመራው የአሜሪካ ልኡካን ቡድን ከግብጹ ፕሬዚዳንት ጄ/ል አልሲሲና የውጭ ጉዳይ ም/ሩ ሳሜ ሹክሪ ጋር የተቃደው ስብሰባ መፈጸሙ የተገለጸ ቢሆንም ከምን አንጻር ሊስተካከል እንደቻለ ግን የተገለጸ ነገር የለም።

የቀድሞ መከላከያ ም/ር የሆኑት ጄ/ል አልሲሲ ስልታዊ በሆነ መፈንቅለ መንግስት በህዝብ የተመረጡትን የሙስሊም ወንድማማቾች መሪ የሆኑትን ፕሬዚዳንት ሙሪሲን ከስልጣን አውርደው ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ በግብጽ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ረገጣን ይፈጽማሉ እየተባሉ በሰብዓዊ መብት ተማጓቾች በተደጋጋሚ ሲከሰሱ የነበሩና በኦባማ አስተዳደር ወቅት ጀርባ ተሰጥቷቸው እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት ጨፍግጎ የነበረውን የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት በሚያሻሽል መልኩ አሜሪካ በአፍሪካ ያለውን አሸባሪነት ከግብጽ ጋር ሆና ትዋጋለች በማለት አዲስ ግንኙነት እንደጀመሩ ይታወቃል። ዋይት ሀውስ ከዛሬው ስብሰባ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ማክሰኞ እለት ለግብጽ ወታደራዊ ተቋም ሊሰጥ የወሰነውን 100 ሚሊዮን ዶላር መሰረዙን እና ሌላ 200 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ እንዳይለቀቅ መያዙ ካይሮን ክፉኛ እንዳሳዘነ የግብጹ የውጭ ጉዳይ ም/ር ለአሜሪካን ልኡካኖች የገለጹ ሲሆን “ውሳኔው መሰረት የለሽ ነው” ብለዋል።

በአፍሪካ ካሉት ሀገራት ውስጥ የአሜሪካንን እርዳታና ድጋፍ በዓመት ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በመቀበል አንደኛ ስትሆን ከዚህ ውስጥ 1.3 ቢሊዮን ዶላሩ ለወታደራዊ ግልጋሎት ተብሎ እንደሚሰጣትና 250 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ ለኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ተብሎ የሚሰጣት ሀገር እንደሆነች ተገልጾ የትራምፕ ልጅ ኢቫንካ ባለቤት የሆነው ጃሬድ ኩሽነር በካይሮ መገኘት ከ2014 ጀምሮ ተቋርጦ የነበረውን የእስራኤልና ፍልስጥኤም ድርድርን ነፍስ ዘርቶ ለመጀመር ነው ተብሏል።