በጅማ የቦምብ ጥቃት ተፈጸመ፤ ከ10 በላይ ሰዎች ተጎድተዋል

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በጅማ ከተማ የተጣለ ቦምብ በሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱ ታውቋል። ጥቃቱ በአንድ ግለሰብ እንደተፈጸመም እየተነገረ ይገኛል።

ይህ የቦምብ ጥቃት የደረሰው ምን ምክንያትን ተመርኩዞ እንደሆነ የሚደረገው ማጣራት እየቀጠለ እንደሆነም ለመረዳት ተችሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ ከተሞች የህዝብ አመጽና የስራ ማቆም አድማ በድጋሚ እንደተጋረጠበትም ዘገባዎች ያመለክታሉ። በባህር ዳርና በጎንደር ከተሞች በተለያዩ ጊዜያት የአገዛዙ ባለስልጣናት ንብረት ናቸው ተብለው በሚታወቁ ድርጅቶች ላይ የቦምብ ጥቃቶች ሲደርሱ እንደነበረም ይታወቃል።

በጅማ ከተማ የፈነዳው ቦምብ በፎቆች መካከል የተወረወረ እንደነበረም የአይን እማኞች እየገለጹ ይገኛሉ። በዚህ የቦምብ ጥቃት የተጎዱ ሰዎች ወደ ጅማ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ለህክምና እርዳታ ሲጓጓዙ እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል።

በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞችና በባህር ዳር አገዛዙን በመቃወም የተለያዩ የስራ ማቆምና የቤት ውስጥ አድማ መጠራቱ ምን አልባትም ከዚህ ጥቃት ጋር ሊገናኝ ይችላል የሚል አስተያየት እየተሰነዘረ ይገኛል።