በኦሮሚያ ክልል ከተሞች ወጣቶች እየታሰሩ ቢሆንም የተጠራዉ ከቤት ያለመዉጣት አድማው ግን ተጠናክሮ ቀጥሏል

0

ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን የያዘዉና በኦሮሚያ ክልል  ለአምስተ ቀናት የተጠራዉ  ከቤት ያለመዉጣት አድማ በኦሮሚያ ከተሞች እና ባንዳንድ ያማራ ክልል ከተሞች ዉስጥ ተጠናክሮ መቀጠሉን ከስፍራዎቹ ያገኘናቸዉ መረጃዎች ሲያመለክቱ ያገዛዙ ታጣቂዎች ወጣቶችን ከየመንገድ እና ከየቤቶቻቸዉ እየያዙ ማሰር መጀመራቸዉንም ለማወቅ ተችሏል። ከትላንት ማምሻዉን ጀምሮ ከሱሉልታ እና በአንቦ ወጣቶች ከየቤቶቻቸዉ እየተወሰዱ እንደሆነና በሻሸመኔ እና በዝዋይ ፖሊሶች ወጣቶችን ሲደበድቡ መታየታቸዉን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

ፖሊሶች ወደ መኖሪያ ቤቶች እየገቡ መታወቂያ ሲመለከቱ እና የሌላ ክልል ነዋሪ የሆኑ ነዋሪዎችን  ሲያስሩም እንደነበርም ታዉቋል። በኦሮሚያ ክልል የሚያልፉ መንገዶችም ሙሉ በሙሉ ዝግ መሆናቸዉን እና አድማዉን ወደጎን በመተዉ ለማለፍ በሚሞክሩ መኪኖች ላይ ቀላል እና ከባድ ጉዳት እየደረሰም እንደሆነ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

አዲስ አበባ አዉቶቡስ ተራ እና መነሀሪያ ወደ ኦሮሚያ ክልል የሚጓዙ መኪኖችም ሆኑ ተሳፋሪዎች ፈፅሞ እንደማይታዩ እና ወደሌሎች ክልሎች የሚደረገዉም ጉዞ እጅግ ቀዝቃዛ መሆኑን በስራዉ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ተናግረዋል። እንዲሁም ዛሬ አርብ የጁማ ስግደትን ሊሰግዱ ወደ መስጊድ የሚገቡ ግለሰቦች ላይ ከባድ ፍተሻ ሲካሄድ እንደነበረ እና መርካቶ አካባቢ በርካታ ቁጥር ያላቸዉ መከላከያዎች መስተዋላቸዉን  ያዩ ነዋሪዎች አገዛዙ እየተደረገበት ባለዉ ተቃዉሞ ከፍተኛ ስጋት ዉስጥ እንደገባ አመላካች ነዉ ሲሉ ይገልፃሉ።

በተያያዘ ዜናም በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች  የግብሩን ጭማሪ በመቃወም ተካሂዶ በነበረዉ የሱቅ መዝጋት ተቃዉሞ ንዴት ዉስጥ የገባዉ የክልሉ አገዛዝ ነጋዴዎችን እና ነዋሪዎችን በማሰርና በማጉላላት ላይ እንደሚገኝም እየተገለፀ ነዉ። በአብዛኛዎቹ የአማራ ክልል ከተሞች የመብራት እና የዉሀ ችግር፣ የነጋዴዎች አመፅ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ተባብሶ እንደሚገኝ እየተጠቀሰ ሲሆን፣ በወልድያ እና አካባቢዉ ካለፈዉ እሁድ ነሀሴ 14 ቀን ጀምሮ እስከ ሀሙስ ነሀሴ 18  ቀን ድረስ ነዋሪዉ በጨለማ ዉስጥ መክረሙን ነዋሪዎች ለትንሳኤ ራዲዮ ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል።    

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ለአምስት ተከታታይ ቀናት ጠፍቶ የነበረዉ መብራት  በመሀከል እለተ ማክሰኞ ምሽት የአሸንዳ በአል አከባበር ከመቀሌ በቀጥታ ስርጭት ይተላለፍ በነበረ ሰአት ተለቆ  እንደነበር እና ስርጭቱ ሲጠናቀቅ ተመልሶ መብራቱ መጥፋቱን ተናግረዋል። አክለዉም አንዳንድ ለስርአቱ ቅርበት ያላቸዉ እና ግብር እንዲከፍል ነጋዴዉን እንዲያግባቡ ተልዕኮ ተሰጥቷቸዉ የነበሩ ግለሰቦች ግብር የማትከፍሉ ከሆነ መብራት ብቻ ሳይሆን ገና ዉሀም ትከለከላላችሁ  ሲሉ መደመጣቸዉንም ተናግረዋል።

በወልድያ እና አካባቢዉ የመብራት መቋረጡ ምክንያት፣ ያለፈዉ አመት ባህር ዳር ላይ በግፍ  ለተጨፈጨፉት ወጣቶች አንደኛ አመት መታሰቢያ እና የግብሩን ጭማሪ በመቃወም  ከነሀሴ 1 እስከ ነሀሴ 3 ድረስ ተደርጎ ለነበረዉ የሱቅ መዝጋት ተቃዉሞ የበቀል ምላሽ ነዉ ሲሉ ነዋሪዎች ይናገራሉ። አክለዉም መብታችንን ስለጠየቅን ብቻ የበቀል እርምጃ የሚወስድብን አገዛዝ እስኪወገድ መታገል እንደሚገባን አገዛዙ እራሱ እያመላከተን ነዉ በማለት ተናግረዋል።