አዲስ አበባ ዉስጥ በሚገኙ መገበያያ ቦታዎች የሚሰሩ ነጋዴዎች እየተፈናቀልን እና በአገዛዙ ንብረታችንን እየተዘረፍን ነዉ ሲሉ አማረሩ

0

መረጃዉን ለዝግጅት ክፍላችን ያቀበሉን ነጋዴዎች ሀና ማርያም ጉልት እየተባለ የሚጠራዉ እና የአካባቢዉ ነዋሪ ለረጅም አመታት ሲገበያይበት የነበረዉን ገበያ ግብር አልከፈላችሁም፣ ህገወጥ ናቹሁ በማለት  የመገበያያ ቦታቸዉ ፈርሶባቸዉና ንብረታቸዉም ተወስዶባቸዉ ፖሊስ ጣቢያ በመመላለስ ላይ መሆናቸዉን በምሬት ገልፀዋል። የአገዛዙ የቅርብ ሰዎች ከፖሊሶች ጋር በመምጣት ነጋዴዎቹ ከገበያ ቦታዉ እንዲወጡ ካደረጓቸዉ በሗላ ንብረቶቻቸዉን እና ሸቀጦቻቸዉን በመኪና እየጫኑ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዱባቸዉ ተናግረዋል።

ንብረቶቻቸዉን ለመከላከል ሙከራ ያደረጉ ነጋዴዎች ታፍሰዉ ተወስደዉ በእስር ላይ እንደሚገኙና በአሁኑ ሰአት እንደ አትክልት እና ፍራፍሬ የመሳሰሉ የነጋዴዎቹ ሸቀጦች በአካባቢዉ በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች ዉስጥ በመበላሸት ላይ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

በገበያዉ ቦታ ላይ ከ2 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ይተዳደሩበት እንደነበር ሲታወቅ ገበያዉ በመነሳቱ ነጋዴዎች ብቻ ሳይሆኑ ያካባቢዉ ነዋሪዎችም ለመገበያየት ረጅም ርቀትን እንዲጓዙ ሆነዋል በማለትም ይገልፃሉ።

በመንደር ዉስጥ በመመስረት ለአካባቢዉ ነዋሪ ግልጋሎትን እየሰጡ ረጅም አመትን ያስቆጠሩ አነስተኛ እና ትላልቅ የገበያ ቦታዎችም በቀጣይነት ይፈርሳሉ ተብሎ እየተሰጋም እንደሆነ ሲጠቀስ ባለፈዉ ሳምንት መገነኛ አካባቢ የነበረዉና ሾላ በመባል የሚታወቀዉ ከ 50 አመታት በላይ ያስቆጠረዉ ገበያ መፍረሱን መዘገባችን ይታወሳል።