ሰሜን ኮሪያ በጃፓን ግዛት ላይ ተምዘግዛጊ ሚሳይል ተኮሰች፣ ፔንታጎን በአስቸካይ ስብሰባ ላይ ነው

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያና አባሪዎቿ ታላቅ የተባለውን የጦር ልምምድ በሰሜን ኮሪያ ወሰን አቅራቢያ እያደረጉ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ሰሜን ኮሪያ ዛሬ በጃፓን ግዛት ላይ ተምዘግዝጎ ያለፈን ሚሳይል መተኮሷን CNN በሰበር ዜናው ገለጸ።

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ ሰሜን ኮሪያ በተመሳሳይ ሁኔታ መካከለኛ ርቀት ተምዘግዛጊ ሶስት ሚሳይሎችን የተኮሰች ሲሆን የዛሬው ባሊስቲክ ሚሳይል 2,700 ማይልስ በጃፓን ግዛት ላይ ተምዘግዝጎ ያለፈ እንደነበረ ደቡብ ኮሪያ የገለጸች ሲሆን ፔንታጎንም ድርጊቱ መፈጸሙን ማረጋገጡን አሳውቋል።

የጃፓንን ግዛት አልፎ በሰሜን ፓስፊክ ውቂያኖስ ላይ የወደቀው የዛሬው የሰሜን ኮሪያ ሚሳይል ጃፓንን እና ደቡብ ኮሪያን እጅግ ያስደነገጠ ሲሆን ሁለቱም በአንድ ድምጽ ድርጊቱ ለደህንነታቸው አስጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

የደቡብ ኮሪያ የጸጥታ ጉዳይ ባለስልጣናት ሶል ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ሲቀመጡ ዋሽንግተን ላይ ደግሞ የፔንታጎን ባለስልጣናት በተመሳሳይ አጣዳፊ ስብሰባ መሰየማቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በሰሜን ኮሪያና በአሜሪካን መካከል በኒውክሌር ውዝግ እየተካረረ የመጣው ሁኔታ ወደ አስጊ ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑ እየታየ ነው።