እውነት አገራችንን መውደዳችንን የምንገልፅበት መንገድ ልባዊ ነው? አገርን መውደድ፣ በባንዲራ ተጎጎናፅፎ ከመታየት በእስክስታ ከመውረግረግ እና ከመሳሰሉት ልቆ አይሄድምን? የህዝባችንን ነፃነትና የሀገራን ህልውና በሚመለከት ድርሻችንን እስከየት ድረስ ነው? አሁን ላለንበት አስከፊ ሁኔታ ተጠያቂው ዉያኔ ብቻ ነው?

ጎበዝ አገርቤት ያሉት ሁኔታዎች እጅግ መረር ብለዋል ። ጎንደር፣ ጎጃም፣ አምቦ፣ ሀረር በሌሎችም አካባቢዎች ጎመራው ፈንድቷል። ነብስ በዚህም በዚያም እየወደቀ ነው። የኛን ዲያያስፖራ ተብዬዎችን ቀልብ ባያሌው እየሳበ ያለው ግን ጠላት በየርከኑ እየመጠነ የሚሰጠን የቤት ስራ ነው። አንዱ ተነስቶ በሽጉጥ ያስፈራራናል- ሳምንት ሁለት ሳምንት ካንድ ድኩም ጋር ስንላላፋ እንውላለን። አንድ አትሌት ተሸነፈች- እንደታምር ለራሳችን አጀንዳ አድርገነው እንሰነብታለን። ኦቦ ጃ ..አንድ ሁለት መስመር ይለቅብንና ያንድ የ3 ሳምንት ስራ ሰጥቶን ዞር ይላል። እኛ እሷን ይዘን ስንንጋጋ እሱ የራሱን ስራ ይስራል።

አሁን አሁንማ ሰልፉም፣ ሻማ ማብራቱም ቀርቷል።

ጎበዝ ትግሉን መርዳት ቀርቶ በሚገባ የተረዳነው አይመስለኝም። በእንቶ ፈንቶው ስንባዝን ከርመን ፈጣን ለውጥ እንጠብቃለን። እየታገሉ ያሉት ሳይደክማቸው እኛ እንዝላለን። እየተጠበሱ ያሉት ትንፍሽ ሳይሉ በረዶ ውስጥ ሆነን እንጨሳለን።

ጎበዝ እየታገሉ ያሉቱ እንደ ቀድሞ ተጋዳላዮች አረብ ገንዘብ የሚያንቆረቁርላቸው፣ የፈረንጅ  ግብረሰናይ ቸብችበህ ታጠቅ ብሎ እርዳታ የሚያዥጎደጉድላቸው፣ ወፍራም ማኮብኮቢያ ጎረቤት ያላቸው አይደሉም። መነሻቸው ከ20 ምናምን አመት በፊት ክ/ሀገር ከነበረች እና በማእቀብ ከደቀቀች ምስኪን አገር ነው።

ተጋዳላዮቹ የታገሉት አለም ፊት ከነሳው፣ በያቅጣጫው ያለረፍት ጠላት ከበዛበት ስርአት ጋር ሲሆን የኛ ታጎዮች እየታገሉ ያሉት ደግሞ ልእለ ሀያላን በትጋት ከሚደግፏቸው፣ ከነነውራቸው አቅፈው ደግፈው ከሚንከባከቧቸው ፣ ያለማቋረጥ ባፍ ባፋቸው ሚሊዮኖችና ቢሊዮኖችን ከሚጠቀጥቁላቸው፣ እድል  ፈልጋ አፈላልጋ ሎሌ ከሆነችላቸው እኩያን ጋ ናቸው።

የወያኔ ደጋፊዎች ቦርሳቸው ነጥቦ፣ መቀነታቸው ተራቁቶ፣ ከጣታቸው ቀለበቱን፣ ካንገታቸው ሀብሉን የሚያበረክቱ፣ ደም የመስጠት ያክል የሚለግሱ ናቸው። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ወንዶቻቸው እጆቻቸው እስኪጓጉሩ የአረብ ቢሮ አፅድተውና ተገርደው፣ ሴቶቻቸው ማዲያት እስኪያወጡ አረቄና ሻይ ቸብችበው  ሲልም ገላቸውን ቸርችረው ነበር።

ይሄን ሁሉ ሲያደርጉ  እንደኛ በደረሰባቸው በደል ሳይሆን፤ ባልኖሩበት ዘመን ተደረገ ተብሎ በተነገራቸው ልቦለድ ሆድ ብሷቸው ነበር።

እነሱ ጋ ትግል የሙሉ ጊዜ ስራ ነው(አሁንም እየታገሉ ነው)።ዝንፍ የለም። ለኛ በእንያንዳንዱ ውሎ የሚወረውሩልን አጀንዳ አያጡም። እንደሸማኔ መወርወሪያ እዛና እዚህ ሲያባክኑን ይውላሉ። አንዳንዴም በራሳችን አጀንዳ ያሳድዱናል። በውነቱ ያሳዝናል። ባህሪያችን ላይ የሆነ የተዛባ፣ ግን ያላወቅነው ነገር ያለ ይመስላል።

ጥቂቶች ቤተሰባቸውን ጣጥለው፣ ሀብት ንብረታቸውን ትተው ድሩን ቤቴ ብለው በረሀ ወርደዋል። ወጣት አርበኞች ለሀገራቸው ና ለወገናቸው ሲሉ፤ ለማይኖሩበት ነፃነት  ለመሰዋት መስመር ላይ ይገኛሉ። የነሱ አካል የሆኑ ካገር አገር እየተንከራተቱ ለራሳችን ነፃነት እኛኑ እየለመኑን ይገኛሉ። ሞልቶን ከተረፈንና ከማንፈልገው ሳንቲም ትግሉን ለመደጎም  ዳተኞች ሆንናል። ለነፃነት ትግል ጥቂት ለማድረግ የምንንቆጠቆጥ ፤ ብዙዎቻችን ለማናውቀው የልደት ቀናችን ያለስስት በስተርጅና ስንመዠርጠው እንታያለን።  በአመት አንድ ጊዜ ለሚደረግ ዝግጅት ላለመገኘት የማንቆልለው የምክንያት አይነት የለም። እሱ ብቻ አይደለም ተቃዋሚ ነኝ እያለ የሚያደነቁረን ሁሉ የሚበረታው እኒሁ ላይ ነው። ሲፈላሰፍ የምናዬው፣ ደርሶ ጋዜጠኛ ነኝ ባዩ፣ አክቲቪስት ነኝ ብሎ በየምናምኑ መስኮት የተሰየመው፣ ሲጨፈጭፍ ከርሞ ከኔ በላይ ታጋይ የለም ባዩ ሁሉ እነሱን ለማሰናከል ሲሆን እንቅልፍ የለውም ። ወያኔን በደንደሱ፣ ታጋዮችን በስሉ አይነት ነገር ነው ሰርክ እያየን ያለነው።

እና በጠላት ላይ ብቻ እንዴ መፍረድ ይቻላል?