የሰሜን ጎንደርን በሶስት ዞን መክፈል በሕዝቡ ቁጣ አስነሳ ተባለ፣ የሱዳን ጦር ዛሬም አለ ተባለ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የአማራ ክልላዊ መስተዳድር ሰሜን ጎንደር ተብሎ የሚታወቀውን ዞን በአዲስ ሶስት ዞኖች ለመክፈል መወሰኑ በነዋሪው ዘንድና በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣና ተቃውሞ ያስነሳ ሲሆን ድርጊቱም “የታላቂቷ ትግራይ” ምስረታ ማወጂያ አካል ነው ሲሉ ገልጸውታል።

በህወሃት መራሹ መንግስት በአሁኑ ሰዓት በጎንደር ላይ እየተካሄደ ባለው የአዳዲስ ድንበሮችና ዞኖችን የመፍጠር ተግባር ላይ የተጠናቀረው ልዩ ዘገባ እንደሚከተለው ቀርባል፣

**ጎንደርን በመከፋፈል የማዳከሙ ሴራና ዓላማ

እንደ የአማራ ክልላዊ መስተዳድር ባለስልጣናት መግለጫ ሰሜን ጎንደር ዞን በይዘቱና በስፋቱ በእጅጉ የተለቀ በመሆኑ ለአስተዳደርና ለልማት አልተመቸም በማለት ዞኑን በሶስት ለመክፈል መወሰኑን ሲገልጽ የአከባቢው ነዋሪዎች ደግሞ “የለም ይህ እኛን ለመጥቀም ተብሎ የታሰበ እርምጃ ሳይሆን ሆን ተብሎ እኛን በማዳከም ለምና ውሃ ገብ የሆነውን መሬታችንን ወደ ትግራይ ለማከተት ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

ክልሉ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ የሆነ ህዝባዊ ጥያቄዎች የተነሱበትና ብሎም ሰፊ የአመጽ እንቅስቃሴዎች የተስተዋሉበት እንደሆነ ይታወቃል። በዚህም ብዙዎች ታስረዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ ተገድለዋል ተብሎ ይነገራል። ያም ሆነ ይህ ሰሜን ጎንደር ዞን በአንድ ወር ግዜ ውስጥ በማንነቷና በግዛቷ ላይ ሁለት ስር ነቀል ለውጥ የሚያመጣ ውሳኔ በፌዴራሉ መንግስትና በክልሉ መስተዳደር የተወሰነባት ክልል ለመሆን ተገዳለች።

የቅማንት የማንነት ጥያቄን ለመመለስ በሚል በፌዴራሉ መንግስት ውሳኔ ሰጭነትና በክልሉ መስተዳድር ተግባሪነት በ12 ቀበሌዎች ውስጥ ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ መጀመሪያ የተወሰነ ሲሆን ለጥቆ ደግሞ ከሁለት ቀን በፊት አጠቃላዩን ሰሜን ጎንደር ዞንን በሶስት የመክፈል ውሳኔ የተላለፈባት ልዩ ዞን ሆናለች።

“በጎንደር ቅማንት ብቻ ሳይሆን አማራው፣ ሽናሻው፣ ቤተእስራኤሉ፣ ጉሙዙና አገው በአንድነትና በፍቅር የሚኖሩባት የቤጃ [በጌምድር] ጎንደር ክፍለ ሀገር ተብላ ነው ይምትጠራው” የሚለው ጎንደር ሕብረት በመግለጫው ዛሬ የጎንደር ሕዝብ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ጥያቄን በይፋ ስላንቀሳቀሰ በቅማንት ህዝብ ስም መሬቱን ወደ ትግራይ ለማጠቃለል መነሳቱን የምንቀበለው ዓይደለም ሲል ይገልጻል።

በትግራይ ሽሬ እንደስላሴ እና በመቀሌ ዋና ጽህፈት ቤት ከፍተው ቅማንት ያልሆኑ የትግራይ ተወላጆች በቅማንት የማንነት ጥያቄን የሚያንቀሳቅሱ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። በቅማንቱና በአማራው መካከል ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን የእርስበርስ ትስስርና የአብሮነትን ታሪክ ሆን ተብሎ በተቀነባበረ የካድሬዎች ዘመቻ ልዩነትን በመፍጠር መልሶ መፍትሄ አቅራቢ ሆኖ መቅረብን ከትግራይ ጥቅም አንጻር እየተካሄደ ያለ አደገኛና መርዘኛ የሆነ ተግባር ሲሉ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

ክልሉ በአዳዲስ ዞኖች እንዲከፋፈልና ብሎም የቅማንት ማንነት ሕዝበውሳኔ እንዲካሄድ የተወሰነበት ከመሆኑም ባሻገር በቋራ ንፋስ ገበያ ባለው ለም መሬት ላይ አንድ ክፍለ ጦር ሰራዊት ከሱዳን መጥቶ የሰፈረበት መሆኑን ነዋሪዎቹ በመናገር “ጎንደርን ከሱዳን የሚያዋስናትን ግዛት በአጠቃላይ ለሱዳን እና ለቤኒሻንጉል በመስጠት ለትግራይ ሊያስተላልፉ ነው” በማለት በስፍራው እየተካሄደ ስላለው ከበድ ያሉ ተግባሮች ይናገራሉ።

ገዢው የህወሃት ስርዓት የታላቋን ትግራይ መንግስት ግንባታ ላይ ነው የሚል ሀሜታና ነቀፋ መሰማት ከተጀመረ እጅግ የቆየ ቢሆንም እንዲህ እንደዘንድሮ ግን በገሃድ ደረጃ ተፈጻሚነቱ ሲታይ አልተስተዋለም ነበር።

በዚህ ሰምንት ብቻ በሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካርታ ከትግራይ ጋር በማገናኘት የአማራውን ጎንደር ከሱዳን የሚያዋስነውን ምእራባዊ ግዛትን የነጠቀ ሆኖ በመገኘቱ ብዙዎች የወደፊታቸው ፕላን ነው ሲሉ በስፍራው ያለው ህዝብ ደግሞ “የለም ዛሬ በዞን መከፋፈልና በቅማንት ማንነት መልስ ሕዝበውሳኔ ስም እየተተገበረ ያለ” ሲሉ ይናገራሉ።

በጎንደር ለም መሬት ላይ የሰፈረው የሱዳን ሰራዊትን በተመለከተ የፌዴራሉ መንግስት በሁለቱ ሀገራት መካከል የጋራ ጸጥታና ደህንነት ለመጠበቅ የተሰማሩ ናቸው ብሎ የገለጸ ሲሆን በስፍራው የሚኖረው ህዝብ መጤው የሱዳን ሰራዊት ገበሬዎችን እያፈናቀለና በምትካቸውም ሱዳናዊን በማስፈር ከመጠበቅ በቀር የሚሰራው ሌላ ስራ አላየንም” ሲሉ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ የሱዳንን መከላከያ ሰራዊት እርዳታ የምትፈልግበት ምን ችግርና የአቅምስ እጦት አጋጥሟት ነው የሚለው በአካባቢው የሚንቀሳቀስ ታጋይ “መሬት በመዝረፍ የተካነው የህወሃት መንግስት የጎንደርን ለም መሬት ለሱዳን፣ ለቤኒሻንጉል ክልልና በቅማንት ስም ለራሱ ለመዝረፍ ያቀደውን ዓላማ ለመተግበር ድጋፍ ፈልጎ ነው” ሲል ይናገራሉ።

በህወሃት መራሹ መንግስትና በሱዳን መንግስት መካከል ከፍተኛ የሆነ ምስጢራዊ ወዳጅነት እንዳለ ይታወቃል። የሱዳን ሰራዊትም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ለምን ማስፈር እንዳስፈለገ ለህዝብ እንዳልተገለጸም ይታወቃል። ነጻ የመገናኛ አውታሮች ክልሉን እንዳይጎበኙ ታግደዋል። የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በከፊል ኢትዮጵያ ብቻ የተነሳ ይመስል ሰሜን ጎንደርና አካባቢዋ ዛሬም በወታደሮች የተወረረች መሆኗን ነዋሪዎች ይናገራሉ። የክልሉ ባለስልጣናት፣ ካድሬዎችና ከትግራይ መጡ የተባሉ ልዩ ነጭ ለባሾች የቅማንትን ማንነት ለመመለስ አጀንዳን ለማስፈጸም በክልሉ ሲርመሰመሱ መታየታቸውን የሚገልጸው መረጃ በርካታ ነው።

የጎንደር ሕብረት ድርጊቱን ከጎንደር አንጻር ብቻ እንዳላየው ካወጣው መግለጫ መረዳት ይቻላል። “ኢትዮጵያን አፈራርሶ የታላቂቷን ትግራይ ግዛትን የማስፋፋት ተግባር “ሲል በአሁኑ ሰዓት በሰሜን ጎንደርና በአካባቢዋ እየተካሄደ ስላለው ተግባር የገለጸ ሲሆን ነዋሪው ግን ዓላማው አይፈጸምም በሚለው አቋሙ ለመጋፈጥ መወሰኑን ነው የሚናገረው።

በተከታታይ የሕዝብን ጥያቄ ባለመስማትና ብሎም ለመመለስ ባለመፈለጉ የሚተቸው የፌዴራሉ መንግስትና የክልሉ መስተዳዳር በዚህኛው ጉዳይ ላይ የህዝብ ቅሬታና ተቃውሞ ያሳሰባቸው ባለመመስል ለተግባራዊነቱ ሲጥሩ እየታየ ሲሆን በሕዝቡ በኩልም ባለመስማማት አቋሙ እንደጸና ሁኔታውን ሲጠባበቅ ይታያል።

ሰሜን ጎንደር የኢትዮጵያን ህልውና በሚያናጋ መልኩ የህወሃት ተግባራት መፈጸሚያነት የተመረጠች ይመስል በርካታ ውስብስብ ተግባራት እየተስተናገዱባት የሆነች ክልል መስላለች።