የኬኒያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንታዊ ውሳኔን ውድቅ አደረገ-ለተቃዋሚዎች ታላቅ ድል ነው

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የኬኒያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት በተቃዋሚው ናሳ[NASA]ፓርቲ የቀረበለትን የምርጫው ውጤት ተጭበርብራል ክስ በመቀበል አጠቃላይ የምርጫው ውጤት ውድቅ ሆኖ ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ የወሰነ ሲሆን ውሳኔው ለተቃዋሚው ታላቅ ድል ሲሆን ለገዢው ፓርቲ ደግሞ ሁለተኛ ዙር ታላቅ ዘመቻን ከወዲሁ ያስጀመረ ልዩ ታሪካዊ ውሳኔ ሆናል።

image
በዛሬው የኬኒያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ታሪካዊ ፍርድ ዙሪያ የተጠናቀረውን ልዩ ዘገባ እንደሚከተለው አቅርቤያለሁ።

**በአፍሪካ ታሪክ የተስተዋለው ታሪካዊው የኬኒያ ጠ/ይ ፍርድ ቤት እድምታ-

ፕሬዚዳንት ሁሩ ኬኒያታና ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ እጅግ ተናደዋል። “የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ኢ-ፍትሃዊ ውሳኔ ነው” ሲሉ በሰባት ዳኞች የተላለፈውን ፍርድ ቤት ውሳኔን የኮነኑ ቢሆንም አክለውም ሲናገሩ “ሆኖም ውሳኔውን ተቀብለናል” ሲሉ በሚፍለቀለቀው የደጋፊዎቻቸው ንዴት ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ቸልሰዋል።

የዛሬው የፍርድ ቤት ውሳኔ በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ በገዢው ፓርቲ ላይ በመፍረድ የመጀመሪያው ነው ያለኝ የእስታንዳርድ ጋዜጣ የኮስት ቢሮ ሃላፊው ጋዜጣኝ ኦቻሚ ዳዊት “ሀገሪታ ይዛው ያለውን ታሪካዊ ፍትህ እጦትን [Historical Injustices ]አሁን ቀስ በቀስ የማከም ስራ እየጀመረች ነው “ሲል የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እድምታ ግልጾልኛል።

አዲሱ ያኬኒያ ሕገ-መንግስት ማለትም በ2010 በህዝበ ውሳኔ የጸደቀው የሀገሪታን ፍርድ ቤትና የፍትህ መዋቅር እራሱን የቻለ ከዋናው ስራ አስፈጻሚው የመንግስት አካል ተጽእኖ ነጻ የሆነ ሉዓላዊ ፍርድ ቤት ሆኖ የተቃቃመ ቢሆንም በ2013 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውዝግብ ላይ ግን ችሎቱ ይህንን ስልጣኑን አልተጠቀመበትም ያስባለውን ውሳኔ በማስተላለፉ በህዝቡ ዘንድ የእምነት ችግር እንዳጋጠመው የህግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የተቃዋሚው ናሳ መሪ አቶ ራይላ አሞሎ ኦዲንጋ ክሳቸውን በይፋ በከፈቱበት እለት “ጠ/ይ ፍርድ ቤቱ ያለፈና ያደፈ ስሙን የሚያድስበት እድል በድጋሚ ቀርቦለታል። ታሪኩንም ለማደስና ፍትህን ለማስፈን ይህንን ክስ በአግባቡ እንዲዳኝ ከወዲሁ በጥብቅ አሳስባለሁ ” ብለው የነበረ ሲሆን በዛሬው ውሳኔም “በኬኒያዊነቴ ተስፋ እንዳልቆርጥ ያደረገ ፍትሃዊና ታሪካዊ ውሳኔ ሲሉ” የደስታ ሲቃ እየተናነቃቸው ተናግረዋል።
በኬኒያ ሕገ-መንግስት መሰረት አወዛጋቢ የሆነና በጠ/ይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ውድቅ የተደረገ ፕሬዚዳንታዊ ውጤት ፍርድ ቤቱ ውድቅ ከደረገበት ግዜ አንስቶ በ60ቀናት ውስጥ ድጋሚ ምርጫ መካሄድ አለበት በሚለው ደንብ መሰረት የድጋሚው ምርጫ በመጪው ጥቅምት ወር ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ለዚህ ደግሞ ፕሬዚዳንቱና ምክትላቸው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በተሰማ ሰዓታት ቆይታ በሃላ ለተሸበሩት ደጋፊዎቻቸው ማረጋጊያ ዘመቻ እንደጀመሩ ታይተዋል።

image
የኬኒያው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰባት ቀን በፈጀውና ከ50በላይ የህግ ባለሙያዎች በተለያየ ጎራ ተሰለፈው ሲፋለሙ የነበረውን ክርክር መጠቅለያ ውሳኔውን ሲያሰማ በርካታ የምርጫውን ውጤት ውድቅ ለማድረግ የሚያበቃ በርካታ ጥፋትና ስህተቶችን [Irregularities ]ማየቱን በመጥቀስ የምርጫውን አጠቃላይ ውጤት ተዓማኒነትን እንዳጣበት ገልጻል።

የምርጫ ቦርድ [IEBC]በሕገ-መንግስቱ ላይ በሰፈረለት ህገ ደንብ መሰረት የምርጫውን ሄደት እንዳልፈጸመ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማግኘቱን የገለጸው ፍርድ ቤት ውሳኔውን ክማንበቡ በፊት የመሃል ዳኛው ዴቪድ ማራጋ “የአንድ ሀገር ታላቅነትና ህልውና የሚጠበቀው በሕገ-መንግስቱ መከበርና መጠበቅ ላይ ነው” ያሉ ሲሆን አክለውም “የፈሪሃ እግዚአብሔርንም በመጠቀም” በማለት በነሀሴ 8ቀን 2017 የተካሄደው ምርጫ በሕገ መንግስቱ ህግና ደንብ ያልተፈጸመ በመሆኑ ውድቅ ሆናል ያሉ ሲሆን ከሰባቱ ዳኞቹ ውሳኔው 5-2 በሆነ ድምጽ እንደተላለፈም ለማወቅ ተችላል።

በፍርድ ቤቱ ውሳኔ የገዢው ጁብሊ[Jubilee ]ፓርቲ ደጋፊዎችና አባላት ማዘናቸውን ቢገልጹም ውሳኔውን በጸጋ ተቀብለው ለሁለተኛው ዙር ምርጫ እንደሚዘጋጁ የገለጹ ሲሆን ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት በሁለተኛው ዙር ከ70% በላይ ድምጽ በማግኘት እንደሚያሸንፉ በመዛት ዘመቻቸውን ከወዲሁ የጀመሩ ሲሆን የተቃዋሚው ናሳ[NASA]ደጋፊዎችና አባላት በበኩላቸው በደስታ እንደሰክሩ የመሃል ዳኛውን ዴቭድ ማራጋን ሀቀኝነት በማወደስ በሁለተኛው ዙር ምርጫ እንደሚያሸንፉ ዝተዋል።

ሆኖም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ምንም ዓይነት ረብሻም ሆነ ግርግር ሳይፈጥር ተቀባይነትን አግኝታል።