በድሬዳዋ ከተማ በአረፋ በአል አከባበር ላይ የተቃዉሞ ድምፅ መሰማቱን የደረሰን መረጃ አመለከተ

0

ዛሬ በተከበረዉ ያረፋ በአል ላይ፤ በየከተማዉ ከፍተኛ የመከላከያ ና የፖሊስ ጥበቃ ይስተዋል እንደነበር የደረሰን መረጃ ሲያመለክት በተለይ በአዲስ አበባ፤ ወደ አንዋር መስጊድ በሚወስዱ መንገዶች ላይ እና በመስጊዱ አካባቢ ከፍተኛ ፍተሻ እንደነበር ታዉቋል።

በድሬዳዋ ደግሞ የከተማዉ ከንቲባ………..ንግግር ማድረግ ሲጀምር ለበአሉ አከባባር የተሰበሰበዉ ሙስሊሙ ማህበረሰብ እጁን በማጣመር ድምፃችን ይሰማ ሲል የተቃዉሞ ድምፁን እንዳሰማ በቦታዉ የነበሩ ግለሰቦች ለትንሳዬ ዝግጅት ክፍል ገልፀዋል። ምእመኑ ተቃዉሞ በሚያሰማበት ጊዜም በህዝቡ መሀል ተበታትነዉ ጥበቃ ሲያደርጉ የነበሩ ነጭ ለባሽ ፖሊሶች ለማስቆም ሙከራ ቢያደርጉም እንዳልተሳካላቸዉ እና ከንቲባዉ ንግግሩን ባጭሩ እንዲያጠናቅቅ መደረጉም ታዉቋል።

 በድሬዳዋ የዘንድሮዉ የአረፋ በአል አከባበር የአገዛዙ ስጋት በግልፅ የታየበት በመሆኑ ወትሮ ከማለዳ ጀምሮ እስከጠዋቱ ሁለት ሰአት የሚቆየዉ የአከባበሩ ዝግጅት ዘንድሮ ከጠዋቱ አንድ ሰአት ላይ እንዲጠናቀቅ ተደርጓል። ዝግጅቱን ይመሩ የነበሩ ግለሰቦች ፊት ላይም ስጋት ይነበብ እንደበነርም ታዉቋል።

በድሬዳዋ  በሙስሊሙ ማህበረሰብ በአል አከባበር ላይ የተቃዉሞ ድምፅ ሲሰማ ይህ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን ያለፈዉ አመት በተከበረዉ ያረፋ በአል አከባበር ላይም ከፍተኛ ቁጥር  ያላቸዉ ፖሊሶች ተሰማርተዉ እንደነበር ይታወሳል።